ሰላም ሰፍኖ ወደ ቀያቸው በመመለስ የእርሻ መሬታቸውን በሰብል መሸፈን ችለዋል

149

መተማ ነሐሴ 9/2014 (ኢዜአ) በአካባቢው ሰላም ሰፍኖ ወደ ቀያቸው ተመልሰው የእርሻ መሬታቸውን በዘር መሸፈን እንደቻሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ ተፈናቀለው የነበሩ ወገኖች ተናገሩ። 

አርሶ አደር አበበ ብርቄ እንዳሉት በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው ወደ ማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ ወረዳ በመሄድ ተጠልለው ቆይተዋል።

በችግሩ ምክንያት ለሁለት ዓመታት በግብርና ስራቸው ላይ ተፅኖ በመፍጠሩ የእርሻ ማሳቸውን ሳያለሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

መንግስት በሰራው የፀጥታ ማስከበርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ ከግንቦት 22/2014 ዓ/ም ጀምሮ ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ቀያቸው ተመልሰው የግብርና ስራቸውን መስራት በመጀመራቸው በቀጣይ ዓመት በምግብ እህል ራሳቸውን በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተያዘው የመኽር ወቅት በ1 ሄክታር ማሳ ላይ ማሽላ፣ በግማሽ ሄክታር ላይ ደግሞ የበቆሎ ሰብል በማልማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተረጋጋ ሁኔታ መደበኛ የእርሻ ሥራ በመጀመራቸው ቤተሰቦቻቸውን ከእርዳታ ጠባቂነት ለማላቀቅ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተሟላ መንገድ ወደ ቀደመ ኑሯቸው ለመግባትና መለሶ ለመቋቋም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ነው አርሶ አደር አበበ የጠየቁት።

ሌላኛው አርሶ አደር ካሳው አየልኝ በበኩላቸው በአከባቢው ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ቤት ንብረታቸውን አጥተው ለ11 ወራት ተፈናቅለው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በወሰደው ሰላም የማስከበር እርምጃና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

በተፈጠረው ችግር ንብረታቸው በመውደሙ መልሶ ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በ2 ሄክታር መሬት ላይ የማሽላ ሰብል ማልማት መቻላቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ በቀጣይ አመት ከእርዳታ ጠባቂነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የምግብ ዋስትናና የአደጋ መከላከል አስተባባሪ አቶ ዮናስ ሞላልኝ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር 350 አባውራና 150 እማወራዎች ተፈናቅለው እንደነበር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው በተሰራው የሰላም ማስከበርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖች በራሳቸው አቅም ወደ ግብርና ስራቸው መመለሳቸውን ጠቅሰው እስካሁን ባደረጉት ጥረትም ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር መሸፈናቸውን ነው የጠቀሱት።

ከግብርና ባሻገር በአነስተኛ ንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩት ስራ መጀመራቸውን ገልጸው፤ተፈናቃዮቹ የመጠለያና የቤት ቁሳቁስ ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ተመላሽ ወገኖችን ሙሉ በሙሉ ለማቋቋም የመንግስትና የተራድኦ ድርጅቶች እገዛ እንደሚያስፈልጋቸውም አስተባባሪው አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት የጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልማህበርና የክልሉ መንግስት ከ6 ሚሊዮን የሚበልጥ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም