የክልሉ ፋይናንስ ቢሮና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመሩ

68

ሐዋሳ፤ነሐሴ 9/2014 (ኢዜአ)፡ የሲዳማ ከልል ፋይናንስ ቢሮ ናየሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ መርሐ ግብር አከናወኑ።

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 300 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር  አራርሶ ገረመው እንዳሉት አቅመ ደካማና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖችን ማገዝ የዜግነት ብቻ ሳይሆን የህሊና ግዴታም ጭምር ነው።

''እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተጋገዝ አንዳችን ለአንዳችን አለኝታ መሆን ይገባል'' ብለዋል።

ቢሮው በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሁለት አቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ለእያንዳንዳቸው 194 ሺህ ብር በጀት መመደቡን ጠቁመዋል።

ከቤት እድሳቱ በተጨማሪ ህጻናቱ የትምህርት እድል እንዲያገኙ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል።

ሁሉም ህብረተሰብ በአቅራቢያው ያሉ አቅም ደካሞችን እና አረጋውያንን በማገዝ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ አሳስበዋል።

በሲዳማ ክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካይ ማስረሻ ክብረት በበኩላቸው ቁጥራቸው 80 የሚሆኑ ድርጅቶች በክልሉ እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው፤ ድርጅቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርና በቤት ማደስ ስራ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በችግኝ ተካላ መርሐ ግብሩ 3 ሺህ የሚሆኑ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በድርጅቶቹ አማካኝነት መተከላቸውን የገለጹት አቶ ማስረሻ፤ የሁለት አቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ በሚሰራው ስራ ድርጅቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

የቤት እድሳት የተደረገላቸው ወይዘሮ መስከረም አንደሞ ቤታቸው ለኑሮ ምቹ ባለመሆኑ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ቤቱ በአዲስ መልክ ፈርሶ ሊሰራላቸው በመሆኑ ደስታ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ እንዳሉት ቢሮው ለአራት ልጆች ሙሉ ወጪ በመሸፈን ትምህርታቸውን እንደሚያስተምርና አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በክልሉ በተያዘው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለተከላ ከተዘጋጀው 302 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 300 ሚሊዮን የሚሆነው መተከሉን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ችግኞች ውስጥ 6 ሚሊዮን የሚሆኑት  የአቦካዶና ማንጎ ችግኞች መሆናቸውን አመልክተው፤ቀሪውን ሁለት ሚሊዮን ችግኝ  በተያዘው ወር መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉት ውስጥ የዳሌ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሮማን ከበደ እንዳሉት ለተተከሉት ችግኞች አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም