በክልሉ የገጠር መሬት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል ስርዓት ሊዘረጋ ነው

224

ሚዛን አማን፣ ነሀሴ 9/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በገጠር መሬት አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም አዋጅ ለማዘጋጀት ግብዓት መሰብሰብን አላማ ያደረገ የባለድርሻ አካላት ውይይት በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ተዘራ ወልደ ማርያም እንዳሉት ቀደም ሲል በ1997 የተዘጋጀው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ጊዜውን ተከትሎ ማስተካከያ ባለመደረጉ ምክንያት ተግዳሮቶች እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው።

የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ ወቅቱንና ጊዜውን ያማከለ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ተዘራ እንዳሉት አርሶ አደሩ የተሰጠውን መሬት አልምቶ የመጠቀም መብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመረዳት መሬትን እንደፈለገ የማድረግ ሁኔታዎች ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል።

በዚህም መሬትን በአግባቡ ያለመጠበቅና ያለመጠቀም ችግር ጎልቶ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው ሰፊ የእርሻ መሬት ይዘው የማያለሙ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የሚስተዋለውን ክፍተት በመሙላት አግባብነት ያለውን የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ለመዘርጋት አዳዲስ ሀገራዊ ግኝቶችን በማከል የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬው መድረክ እስካሁን ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የቀድሞ የደቡብ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅና ያሉበትን ችግሮች በመለየት ለማሻሻል የሚያግዙ ግብአቶችን ለመሰብሰብ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ ገልጸዋል።

አዲስ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ለማዘጋጀት የሚያስችል ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተደረገ ባለው የውይይት መድረክ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያምና ሌሎች የክልል ከፍተኛ አመራሮችና በፌደራል ግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም