በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የክልሉን ህዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል-ቢሮው

70

አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 09/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ክልል በተጠናቀቀዉ የበጀት ዓመት 305 የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን ግንባታ በማጠናቀቅ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ውሃ፣መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

 የቢሮው ሃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የህዝብ ጥያቄ ሆነው የቆዩ የውሃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ምላሽ ለመሰጠት በልዩ ትኩረት ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም በ2014 በጀት ዓመት 305 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ከ521 ሺህ በላይ የክልሉን ህዝብ  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ''ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሲንከባለሉ የቆዩ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ችለናል'' ብለዋል፡፡

 በተያዘው በጀት ዓመት በጋሞ ዞን ግንባታቸው ተጠናቅቆ በትናትናው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ዘጠኝ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጄክቶችን በአብነት አንስተዋል።

በ2015 የበጀት ዓመት ደግሞ 650 ሺህ ህዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ 445 የንጹህ መጠጥ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በደቡብ ክልል ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን መቶ በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ የተገኘው ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም