በአዲስ አበባ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ243 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኙ

67

አዲስ አበባ ነሃሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በአዲስ አበባ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በ2014 በጀት አመት ከ243 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ።

የኤጀንሲው አማካሪ አቶ መለስ ደምሴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲስ አበባ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ መስፋት እየተከናወነ ነው።

በዚህ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ 2 ሺህ 400 አባላት ያሏቸው 94 ማህበራት መኖራቸውን ገልጸዋል።

የውሃ መያዥ ፕላስቲክ፣ ወረቀት፣ ብረታ-ብረትና ጀሪካን የመሳሰሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማሰባሰብ ለፋብሪካ ያቀርባሉ።

በዚህም በበጀት አመቱ 243 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪዎች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለገቢው መገኘት አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ከተያዘ ሃብት መሆኑን ያሳየም ነው ብለዋል።

በዘርፉ ከተሰማሩት አንቀሳቃኞች መካከል አቶ ተስፋየ ዘነበ፣ አቶ ታምራት አብደላ ናአቶ አለባቸው ይማም እንዳሉት በተሰማሩበት ዘርፍ የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ወላጆቻቸውን ከመደገፍ ባለፈ ቤተሰብ በመመስረት የተሻለ ኑሮ ለመኖር መብቃታቸውን ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ከራሳቸው አልፈውም ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።

በበጀት አመቱ በዘርፉ ከ835 በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ያገለገሉ ዕቃዎችን መልሰው ጥቅም ላይ የሚያውሉ ፋብሪካዎች ለምርት የሚያስፈልጋቸውን ጥሬ ዕቃ ከዘርፉ መረከባቸው ለወጣቶቹ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል ፡፡

በዚህም ፋብሪካዎቹ ለጥሬ ዕቃ ግዥ ያወጡት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን አማካሪው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም