በጋምቤላ ክልል የአሸባሪዎችን የጥፋት እንቅስቃሴ ለማስቆም የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው

153

አዲስ አበባ ነሃሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የአሸባሪዎችን የጥፋት እንቅስቃሴ ለማስቆም የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ተናገሩ።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ተንኳይ ጆክ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪ የሆነውና ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራው የጥፋት ቡድን በክልሉ ሰላም ለማደፍረስ ያደረገው ሙከራ ከሽፏል፡፡

የፌደራል ፖሊስ፣ የጋምቤላ ልዩ ሃይልና ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ ጥምር ሃይል በጋራ በወሰዱት እርምጃ የጥፋት እቅዱን ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊትን የሰሜን ኢትዮጵያ ህግ የማስከበር ተልእኮ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አሸባሪ ቡድኖች በሌሎች አካባቢዎች የጥፋት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አስታውሰው በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ እርምጃ መደምሰሳቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ክልል አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ዜጎች ወደ መደበኛ ሰላማዊ እንቅስቀሴያቸው ተመልሰዋል ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡

በክልሉ የሽብርተኞችና ጸረ ሰላም ኃይሎች መደበቂያ ስፍራዎችና መተላለፊያ ቦታዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከቄለም ወለጋ ተነስቶ ወደ ጋምቤላ ክልል የሚገባው የሽብር ቡድንም በጸጥታ ሃይሉ በተወሰደበት የማያዳግም ርምጃ አካበቢው ነፃ ሆኗል ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት አሸባሪዎችን ለመደምሰስ ትልቅ ስራ ሰርቷል፤ በዚህም የሽብር ቡድኖች ወደ ጋምቤላ ክልል የሚገቡበት እድል የላቸውም ብለዋል፡፡

የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪ የሆነውና ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራው ቡድን በጋምቤላ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ተኩስ በመክፈት በንጹሃን ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም