በሠመራ ሎግያ ከተማ ጎርፍ ባስከተለው አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

243

ሠመራ፤ ነሐሴ 9 ቀን 2014(ኢዜአ) በአፋር ክልል ሠመራ ሎግያ ከተማ ጎርፍ ባስከተለው አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ቢልኢ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አደጋው የደረሰው ትናንት ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ የሎግያ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ አካባቢውን በማጥለቅለቁ ነው።

ከሌላ አካባቢ በጣለው ከባድ ዝናብ ወንዙ በመሙላቱ የወንዙን ግንብ አልፎ ወደ ጀቡቲ በሚወስደው አስፓልት መንገድን አቋርጦ ሲፈስ ማደሩን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ በመንገዱ ላይ የተጥለቀለቀውን የጎርፉን ውሃ በእግራቸው ለማቋረጥ የሞከሩ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።

ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች በውሃው ተወስደዋል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ የጸጥታ ሃይሉና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የማፈላለግ ስራ እያከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም መንገዱን ሲሻገሩ በተወሰዱ ሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ የነበሩ ስምንት ሰዎች በአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና በህብረተሰቡ ርብርብ ህይወታቸውን ማትረፍ መቻሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም