በኦሮሚያ ክልል በምርት ዘመኑ ከ100 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ እየለማ ነው

124

ነሐሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኦሮሚያ ክልል በምርት ዘመኑ ከ100 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ወጪ ምርቶችን መጠንና አይነት ማሳደግና ገቢ ምርቶችን መተካት በሚል መርህ እየተሰራ ይገኛል።

በዚሁ መሰረት በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ምርትና ማርታማነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ አበራ ወርቁ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በ2014/15 የምርት ዘመን በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩዝ ሰብል በስፋት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

የሩዝ ልማቱ በኢሉባቦር፣ ጅማ፣ ወለጋና ቡኖ በደሌ ዞኖች ላይ እየተከናወነ ሲሆን ከታያዘው ዕቅድ በላይ መሬት በሩዝ ሰብል መሸፈኑን ነው የተናገሩት።

በክልሉ እስካሁን በስፋት ያልተሰራበት በሻይ ቅጠል ምርት 2 ነጥብ 5 ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ዓመትም የሻይ ቅጠልን በስፋት በማልማት ወደ ውጭ የመላክ እቅድ እንዳለ ነው የተናገሩት።

ከ1 ቢሊን በላይ የቡና ችግኞችን ለማጽደቅ የተከላ ሂደት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል በምርት ዘመኑ በመኸር 205 ሚሊየን ኩንታልና በበልግ 17 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱታውቋል።