የድርቅ አደጋ በእንስሳት ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል በመስኖ የመኖ ልማት ስራ እየተከናወነ ነው- የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ

123

ነሐሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድርቅ አደጋ በእንስሳት ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል መኖ በመስኖ እየለማ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው አስከፊ ድርቅ በርካታ የእንስሳት ኃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ይታወቃል።

በመሆኑም የድርቅ አደጋው በእንስሳት ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል በመስኖ የመኖ ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ፤ በተጠናቀቀ በጀት ዓመት በቦረና ዞን ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ቤል  ሳር በመስኖ ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።

በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ በመስኖ ልማት ስራዎች ላይ በማተኮር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የመኖ ልማትን በመስኖ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር፤ በበኩላቸው በ2014 በጀት ዓመት ተከስቶ የነበረው ድርቅ በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ እንስሳት መግደሉን ገልጸዋል።

የድርቁ አደጋ ከ26 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸውን እንስሳት አሳጥቷል ብለዋል።

ከ14 ሚሊዮን በላይ እንስሳትም በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን አስታውሰው በተለይም በቦረና፣ በምስራቅ ባሌና በምስራቅ ሀረርጌ ቆላማ ዞኖች ድርቁ የከፋ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የድርቁን አደጋ ለመመከት የፌዴራልና የክልሉ መንግስት እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል።

በዚህም ከ10 በመቶ በላይ የቦረና ከብት ዝርያዎችን ማትረፍ መቻሉን አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል።

ከክልሉ ሌሎች አካባቢዎች የእንስሳት መኖና ሳር በማጓጓዝ ድርቅ ወደ ተከሰተበት አካባቢ ተደራሽ መደረጉን አስታውሰው አሁን ላይ ግን ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የከብቶች መኖ የማምረት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ሳር በብዛት በማምረት እዛው በማከማቸት ድርቅ ሲከሰት ለመጠቀም የሚያስችል አሰራሮች ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አጠቃላይ ድርቁ በክልሉ የእንስሳት ሃብት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የመኖ ልማት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።