የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከጉባኤዎች ያለፈ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

155

ነሐሴ 09 ቀን 2014(ኢዜአ) አለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉዳዩን የተመለከቱ ጉባኤዎች እና ስብሰባዎች ከማድረግ ያለፈ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመለከቱ።

“የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ለሆነችው አፍሪካ የሚበጀው ችግሩን ማውራት ሳይሆን እንደ አረንጓዴ አሻራ ባሉ መፍትሔ አምጪ ስራዎች ላይ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ ነው”ም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “አገርን አረንጓዴ እያረጉ ያሉ እጆች” በሚል ርዕስ በማኅበረሰብ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ለአለም አቀፉ ባስተላፈፉት መልዕክት በቅርብ ጊዜያት ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተለያዩ ክስተቶችን እያስተናገደች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ጎርፍ፣ሰደድ እሳት፣የሙቀት መጨመር፣የበረሃማነት መስፋፋት እና ሌሎችም ችግሮች አለምን ለአሳሳቢ ሁኔታ እንደዳረጓት ተናግረዋል።

ምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው ድርቅ እንዳጋጠማቸውና በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎችም የከፋ ድርቅ ማስከተሉን አመልክተዋል።

ለበርካታ ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ የተመለከቱ ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ መቆየታቸውን አንስተው አሁን ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ያለበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

“ከጉባኤዎች እና ስብስባዎች ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥ ላመጣብን ፈተና መፍትሔ የሚሆን ተጨባጭ አርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ችግሩን ለመከላከል በሁሉም ደረጃ የሚገኘውን የሕብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል፤ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ስኬታማ ስራ ማከናወን ችላለች ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 በተፋሰሱ አገራት በጎ ተጽእኖ ለማምጣት፣የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ከተማን አረንጓዴ ማልበስ እና ሌሎች ተያያዥ ውጤቶችን ለማምጣት አረንጓዴ አሻራን መጀመሯን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሱት።

በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በመርሐግብሩ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቀዶ 25 ቢሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉንና ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሳታፋቸውን አመልክተዋል።

አረንጓዴ አሻራ የደን መመናመንን በመቀነስ፣አዲስ የደን ሽፋን በመፍጠር እና የአየር ንበረትን ለውጥ ከመከላከል አኳያ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መብዛት፣የችግኝ መትከያ ቦታዎችን ቀድሞ መለየት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት አረንጓዴ አሻራ ስኬታማ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶችን መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

ቀጣዩ ትውልድ የችግኙን ፍሬ እንደሚያይ ምንም ጥርጣሬ የለኝም ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይልን ወደ መጠቀም እየሸጋገረች እንደምትገኝና ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መፍትሔ እንደሚሆን ተናግረዋል።

“የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ለሆነችው አፍሪካ የሚበጀው ችግሩን ማውራት ሳይሆን እንደ አረንጓዴ አሻራ ባሉ መፍትሔ አምጪ ስራዎች ላይ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ ነው” ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ስራቸው እንደ ተሞክሮ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

አፍሪካ እና የተቀረው ዓለም በጋራ በመሆን እንደ አረንንጓዴ አሻራ ያሉ መርሐግብሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም