የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሊጉን አደረጃጀት ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች አበረታችናቸው--የሴቶ ሊግ ፕሬዚዳንት

194

አዳማ ነሐሴ 8/2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት አመት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሊጉን አደረጃጀት ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ገለፁ ።

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የ2014 ዓ.ም የስራ ዕቅድ አፈፃፀምና የአዲሱ በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ላይ በአዳማ ከተማ ውይይት እያደረገ ነው ።

የሊጉ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ እንደገለፁት ባለፈው በጀት አመት ሴቶችን በስልጠና በማብቃት ተሳትፎአቸውንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተሰሩ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በተለይ በህልውና ዘመቻው ላይ ሴቶች የነበራቸው ተሳትፎ፣ የመከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል፣ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎችን ያሉ ሴቶችን በመደገፍና የመተጋገዝ ባህልን በማደበር የተሰሩ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል ።

በተመሳሳይ በዜግነትና በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ እናቶችን ቤት በማደስና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል ።

ሊጉ በብልጽግና ፓርቲ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመፈፀምና በማስፈጸም አደረጃጀቶችን በማጠናከርና የሊጉን አባላትና አመራሮችን በማብቃት በኩል የተሻለ ስራዎች መሰራቱን ተናግረዋል።

የሊጉ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማጠናከር የሚያስችሉ የቁጠባ ባህላቸውን የማጎልበት፣ የስራ ዕድል እንዲያገኙ በማስቻል፣ በትምህርት ተሳትፎና በጤና አገልግሎት ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ስራዎች መሰራቱን አብራርተዋል።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ የአቅም ግንባታ ስራና የመደመር እሳቤን በማስረፅ የተሻሉ ስራዎች መከናወኑን አመላክተዋል ።

የሴቶች ሊግ አደረጃጀቶችን በሚፈለገው ቁመና ላይ በማድረስ በኩል፣ የአቅም ውስንነት፣ የአመለካከት ክፍተቶች በሚፈለገው ደረጃ አለመቀረፋቸውን ወይዘሮ ጠይባ ገልጸዋል ።

በአዲሱ በጀት ዓመት በስራ አፈፃፀም የተለዩ ክፍተቶችንና ጠንካራ ጎኖችን መነሻ በማድረግ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ብለዋል ።

የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ለማሳካት በየደረጃው ያሉ የሊጉ አባላትና አመራሮችም ርብርብ ማድረግ ይገባቸውል ነው ያሉት ።

ውይይቱ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድና በአዳማ ከተማ የሴቶች ሊግ አደረጃጀት የተሰሩ የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት ስራዎች በኮሚቴው እንደሚጎበኙ ተመላክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም