በዞኑ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ ነው -መምሪያው

158

ዲላ ነሐሴ 8/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ከ2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝርያዎች በኩታ ገጠም ማሳ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የዞኑ የግብርና መምሪያ ገለጸ።

በዞን ደረጃ ለእንስሳት መኖ የሚውሉ የተለያዩ የተሻሻሉ የሳር ዝርያዎች ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በዲላ ከተማ  ተካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ  እንዳሉት በዞኑ የእርሻ ልማቱን ከእንስሳት እርባታ ጋር በማቀናጀት እየተሰራ ነው።

የእንስሳት ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፍ የአርሶ አደሩን ገቢና የምግብ ዋስትና ችግር በዘላቅነት ለመፍታት በዞኑ ሁሉም አከባቢዎች ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

የእንስሳት መኖ ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ የተሻሻሉ የሳር ዝርያዎች በስፋት እየተተኩሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከአካባቢው ስነ ምህዳር ጋር የሚስማሙና የንጥረ ነገር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ የመኖ ዝሪያዎች ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

በዞኑ ከ2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመምሪያው የእስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተካዬ ናቸው።

የመኖ ልማቱን በየአካባቢው ከ1 እስከ 5 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ለማልማት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንስሳት አርቢዎችና አርሶ አደሮች ያላቸውን መሬት ተጠቅመው ለእንስሳት የመኖ ምንጭ በመፍጠር የእንስሳት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዲላ ከተማ የኤልኮት የከብት ማድለብያ ማህበር አባል አቶ ወርቁ ሲማ በበኩላቸው ለእንስሳት እርባታ የመኖ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ከብቶችን ለማደለብ የተሻሻሉና የንጥረ ነገር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነ የመኖ ዝርያዎች  ማልማት ለከብቶች ጤንነትም ሆነ ፈጣን ለውጥ በማምጣት በአጭር ጊዜ ለገበያ ለማብቃት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በ5 ነጥብ 5 ሄክታር ማደለብያ መሬታቸው ላይ የተሻሻሉ የመኖ ዝሪያዎችን በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በ1 ሺህ 700 ሄክታር ማሳቸው ላይ ደሾ ሳር፣ ጎት ማላ እንዲሁም ሌሎች የመኖ ዝርያዎች ተከላ ማካሄዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቤቴልሄም አዳኝ ናቸው።

ለሚያረቧቸው እንስሳት የመኖ ችግርን ከመቅረፍ ባለፍ በአካባቢያቸው ለሚገኙ አርቢዎች ጥራቱን የጠበቀ መኖ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት የእንስሳት መኖ ተከላ እንዲሁም የእንስሳት እርባታና የእንስሳት መኖ ልማት ጉብኝት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም