ኢትዮ ቴሌኮም ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት በቴክኖሎጂ እያገዘ ነው

153

ጎባ ነሐሴ 8/2014 (ኢዜአ) ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዲጂታል ላይብረሪ አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በባሌ ሮቤ ጋላማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዲጅታል ላይብረሪ  አገልግሎት በይፋ ስራ አስጀምሯል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ምሥራቅ ሮቤ ጽህፈት ቤት ቀጥታ ያልሆነ የቴሌኮሙኒኬሽን መስመሮች አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ በቀለ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም የመረጃ ልውውጥን ከማሳለጥ በተጓዳኝ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ነው፡፡

ድርጅቱ የተመረጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የዲጂታል ላይብረሪ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ ነው ጥረቱን እያገዘ ያለው።

ለጋላማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተደረገው ድጋፍ የጥረቱ አካል መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው የዲጂታል ላይብረሪው ተማሪዎች ከቴክኖሎጂና ዘመናዊ የትምህርት ቁሳቁሶች ጋር በቅርበት እንዲተዋወቁ ያግዛል ብለዋል፡፡

ለትምህርት ቤቱ ከተደረጉ ድጋፎች መካከል 21 ዴስከ ቶፕ ኮምፒውተሮች፣አንድ የፕሪንተር ማሽን፣ 21 ዘመናዊ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

ለትምህርት ቤቱ የነፃ የብሮድ ባንድ የኢንተርኔት አገልግሎት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው ለድጋፎች 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የመረጃ ልውውጥን ከማሳለጥ ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት በመሳተፍ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ ናቸው፡፡

በተለይ ለትምህርት ቤቱ የዲጅታል ላይብረሪ አገልግሎት ተጠቃሚ መደረጉ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ የዲጂታል ላይብረሪ አገልግሎቶችን በሌሎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ለማስፋት ከድርጅቱ ተሞኩሮ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

የባሌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናስር አህመድ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም እንደ አገር የትምህርት ጥራንት ለማሻሻል እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል።

ተማሪዎች የድጂታል ላይብረሪውን በመንከባከብ እራሳቸውን በእውቀት እንዲያንጹ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በትምህርት ቤታቸው በቂ ኮምፒውተሮች ባለመኖራቸው በሚፈልጉት መልኩ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ይቸገሩ እንደነበር የጠቀሰው የትምህርት ቤቱ ተማሪ ሀሰን ጣህር ነው፡፡

የዲጂታል ላይብረሪው ወደ አገልግሎት መግባቱ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሁለንተናዊ እውቀታቸውን ለማሳደግ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል፡፡