ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ ሰንሰለቱን በማቀላጠፍ የኢትዮጵያን አምራችነት ይበልጥ ያጠናክራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

177

ነሐሴ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ ሰንሰለቱን በማቀላጠፍ የኢትዮጵያን አምራችነት ይበልጥ ያጠናክራል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ነጻ የንግድ ቀጣናው የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው የተገለጸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣናን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ ነጻ የንግድ ቀጣናው የኢትዮጵያን መጻኢ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያግዝ ጅማሮ ነው።
በመሆኑም ባለሃብቱ በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና በመሳተፍ ራሳቸውንና አገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣናው በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ላለው የምርት እድገት ምቹ ገበያ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድሬዳዋና አካባቢውን የኢኮኖሚ ኮሪደር ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም ዛሬ የተመረቀውን ነጻ የንግድ ቀጣና እና የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በአብነት አንስተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የነጻ ንግድ ቀጣናው የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚጠበቅነትን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የገቢና ወጪ ንግድን ለማሳለጥ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።
የነጻ የንግድ ቀጣናው የአቅርቦት ሰንሰለትን በማሳጠር የሎጂስቲክስ ወጪን በመቅረፍ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
ለስራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ ለነጻ የንግድ ቀጣናው የሚሆኑ መሰረተልማት የማሟላቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የህግ እና አሰራር ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም