የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማክሮ ኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው

261

ነሐሴ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)እንደ ሀገር ለተመዘገበው የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የዕድገቱን ዘላቂነት እንዲያስጠብቅ ማጠናከር እንደሚገባ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ፡፡

ምሁራኑ የኢኮኖሚ እድገቱ ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ ስራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

እንደ ምጣኔ ሃብት ምሁራኑ ገለጻ የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /አይ.ኤም.አፍ/፣ አለም ባንክና ሌሎች ድርጅቶች ከሚያወጡት ትንበያ ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አባተ የስጋት እንዳሉት ባለፉት ሶስት ዓመታት እንደ ሀገር ያጋጠሙ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ኢኮኖሚው ላይ ጫና ፈጥረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት አኮኖሚው እንዳይጎዳ መተግበር የጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተመዘገበው የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

የወጭና ገቢ ንግድ አለመጣጣም፣ የብድር ጫናን ጨምሮ ሌሎች በዘርፉ የታዩ በርካታ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ያስቻለው የኢኮኖሚ ማሻሻያው ነው ብለዋል፡፡

የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በጊዜና በራስ አቅም የማጠናቀቅና ምርታማነትን መጨመር ላይ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ላይ የተጀመረው ስራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

''የኢኮኖሚ ዕድገት የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል እንደሚችል ይታመናል'' ያሉት ተመራማሪው፤ ምርታማነትን ማሳደግና አቅርቦት ላይ የሚታየውን ችግር መፍታት የመንግስት ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለዚህም ግብርናውን ማዘመን ቀዳሚ ስራ መሆን እንዳለበትና የተጀመረውን የበጋ መስኖ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ስንዴን ጨምሮ ወደ ውጭ የምንልካቸውን ምርቶች በጥራትና በዓይነት ከመጨመር ባሻገር ሌሎች ዘርፎችን ማሳደግና ባለሀብቶችን ማሳተፍ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

አሁን እየታየ ያለው ለውጥና ዕድገት ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አባተ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የመንግስት፣ የግል ባለሀብቱና አገልግሎት ሰጪው በተቀናጀ መልኩ ተግቶ በመስራት ዘርፉን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት መምህርና ባለሙያ ዶክተር ስንታየሁ ሃይሉ በበኩላቸው ስንዴን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የሚከናወነው የኩታ ገጠም እርሻ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚደረጉ ጥረቶች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም እየታየ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል መንግስት የጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ በመሆኑ የሚያጠናክሩ ተግባራት ማስፋት ላይ መተኮር ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ከግብርናው በተጨማሪም የፋይናንስ ስርዓት ከማዘመን ጀምሮ በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ተስፋ ሰና በሂደት የሚታይ ውጤት የሚያመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የተጀመረው እድገት ውጤታማ እንዲሆን ማሻሻያ የተደረገባቸው ዘርፎችን በተገቢው መከታተል እንደሚገባ ገልጸው፤ቀልጣፋ አሰራር መከተልና ለኢንቨስትመንት ምቹ አካባቢን መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የባንኮችን የብድር መጠን በማሳደግ የግል ባለሀብቱን ማበረታታትና የፋይናንስ አሰራሩን ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ቴሌኮሚኒኬሽንን ጨምሮ የሃይል አቅርቦቱን ለማሳደግ በህዳሴ ግድብ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበትን መከላከል፣የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት በኮቪድና በግጭት ምክንያት የተጎዳውን ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ማሳደግ የሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎችን በተገቢው መልኩ ማከናወን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

እየተመዘገበ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ልክ የዜጎች ገቢ ማደግ እንዳለበት የጠቀሱት ምሁሩ፤ የዋጋ ግሽበቱን በመቆጣጠር የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

የዋጋ ግሽበቱ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ያለውን ማህበረሰብ ተጎጂ እንዳያደረግና እድገቱ ደሃ ተኮር እንዲሆን መንግስት አማራጮችን መጠቀምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት ለተጠቃሚውም ሆነ ለባለሀብቱ ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የጀመረውን ድጋፍ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንደ ምጣኔ ሀብት ምሁራኑ ገለጻ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለተመዘገበው የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ዕድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ደግሞ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ከማምረት ባለፈ አዋጭ የሆኑ ሌሎች ምርቶችን በመፈተሽ ማምረት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም