በኢትዮጵያ 2ሺህ300 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ለመዘርጋት የአዋጭነት ጥናት ተካሂዶ ተጠናቋል

72
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በኢትዮጵያ 2ሺህ300 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ለመዘርጋት የአዋጭነት ጥናት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ብርሃኑ በሻ ከቻይና አፍሪካ አድቫይዘሪ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የባቡር ጉባኤ ዛሬ ሲጀመር እንዳስታወቁት፤ በአገሪቱ በስምንት አቅጣጫዎች 5 ሺህ ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ለመዘርጋት እየተሰራ ነው። ሊገነባ ከታሰበው መስመር ውስጥም የሰውና ይዕቃ ማጓጓዣ ውስጥ የ2 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የአዋጭነት ጥናት፣ የመስመር ዝርጋታ ዲዛይን፣ የአካባቢና የማህበረሰባዊ ተፅዕኖዎች ጥናት መካሄዱን ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመተላለፊያ ፕሮጀክት ልማትና የባቡር ቱሪዝም ፕሮጀክት ጥናቶች መሰራታችውንም ገልፀዋል። 1ሺህ90 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሞጆ -ሞያሌ መስመር፣ 750 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ከባህርዳር-ወረታ-ወልዲያ መስመር፣ 500 ኪሎሜትር የሚረዝመው የአዲስ አበባ-ሰበታ-ጅማ- በደሌ መስመር የሚጠቀሱ ናቸው። የባቡር መስመሮቹ ከአገር ውስጥ ትስስር በተጨማሪ ከሴኔጋል፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር የንግድ ትስስር ለመፍጠር የሚያገለግሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የባቡር መስመሮቹ ግንባታ በመንግስት ወጪ ብቻ መሸፈን ስለማይቻል ከግል ባለሀብቶችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመስራት በጉባኤው ምክክር የሚደረግበት እንደሆነ ዶክተር ብርሃኑ ገልጸዋል። የግል ባለሀብቶችን ወደ መሰረተ ልማት ስራዎች በማስገባት ፕሮጀክት ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመንግስትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑም ተጠቅሷል። የግል ባለሀብቶች በዘርፉ መሰማራታቸው አሁን ላይ እየገጠመ ያለውን የፋይናንስ እጥረት፣ የሀብት አጠቃቀም ችግርና የፕሮጀክቶች መጓተትን እንደሚቀንስ ታምኖበታል። በጉባኤው በባቡር መስመሮችና ተጓዳኝ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ልምድ ካላቸው አለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር የአንድ ለአንድ ውይይትም ይደረጋል ተብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም