በኢትዮጵያ የተከሰተውን ከባድ የድርቅ አደጋ በመመከት ሂደት የምላሽ አሰጣጡ የተሳካ ነበር- ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

166

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተከሰተውን ከባድ የድርቅ አደጋ በመመከት ሂደት የምላሽ አሰጣጡ የተሳካ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።

ሚኒስቴሩ በ2014 ዓ. ም እቅድ አፈጻጸም እንዲሁም በ2015 ዓ.ም መነሻ እቅድ ላይ ከክልል ሴክተር ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

May be an image of 8 people, people sitting and people standing

ምክክሩ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በየዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት የሚካሄድ ይሆናል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፤ ባለፉት 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች ማጋጠሙን አስታውሰዋል።

የድርቁን አደጋ ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ መመከት መቻሉን ገልጸው፤ በምላሽ አሰጣጡ የተሳካ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የውሃ ተቋማት ጥገና፣ የእንስሳት መኖ እና የውሃ አቅርቦት ላይ በተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

ከ1 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ መልማቱን የገለጹት ሚኒስትሯ መኖውን ድርቅ በተከሰተበት አካባቢ በማጓጓዝ ድርቅን መቋቋም መቻሉንም አንስተዋል።

የእንስሳት መኖን አንድ ቦታ አምርቶ ድርቅ ወደ ተከሰተበት አካባቢ ከማጓጓዝ በተጓዳኝ ድርቁ ያጋጠመበት አካባቢ ማምረት ላይም ትኩረት እንደተደረገ ተናግረዋል።

የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ላይ በተሻለ መልኩ መሰራቱን ጠቁመው፤ ይህም ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

አርብቶ አደር አካባቢ ድርቅን ጨምሮ የሚያጋጥሙ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንደተዘጋጁ ጠቁመው፤ በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በመስኖ ልማት 156 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ጠቅሰው፤ ስኬታማ ክንውን ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በመስኖ ልማት በኩል የተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የካሳ ክፍያ ጉዳይና የጸጥታ ችግሮች ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።