አገር የሚያስቀጥሉ ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት ሂደት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

110

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አገር የሚያስቀጥሉ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት ሂደት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ የፓርቲ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ አገር አቀፍና ክልላዊ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከ50 በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያን የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላትን ጎብኝተዋል፡፡

May be an image of 8 people, people standing and indoor

የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ የመረጃ ደኅንነት አገልግሎት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የሳይንስ ሙዚየምና ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀ መንበር ሙሳ አደም፤ ቀጣይነት ያላቸው አገራዊ ተቋማትን መገንባት የአንድ ጀምበር ሥራ ባይሆንም ለትውልድ የሚሻገር ጡብ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አብዱልቃድር አደም፤ የአገርና ሕዝብ ደኅንነትን ለመጠበቅ እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ክፍለማርያም ሙሉጌታ፤ ባለፉት አራት ዓመታት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በምርምር ዘርፍ ትልቅ እምርታ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

ኮርያ 60 ዓመት ባልሞላ ጊዜ የዓለማችን ግዙፍ ካምፓኒዎች ባለቤት መሆን እንደቻለችው ሁሉ ኢትዮጵያም ወደዚያ መንገድ በሚወስዳት ጉዞ ላይ መሆኗን ተረድተናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ዋና ጸሐፊ አበበ አካሉ፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ሀብት የሆኑት የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው በማየታችን ደስ ብሎናል ብለዋል፡፡

May be an image of 1 person

እየተገነቡ ያሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላትም የነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ እንዳላት የሚያሳዩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን እርስ በርስ መገፋፋት በመተው በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ተገንብቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህን ተቋማት የጋራ አገራቸው ተቋማት መሆናቸውን በመገንዘብ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው አገራዊ ተቋማትና ፕሮጀክቶች ላይ አንድ አይነት እይታ ሊኖራቸው ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ አገር የማስቀጠል ራዕይ ባላቸው ተቋማት ላይ አንደራደርም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም