የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎበኙ

109

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ አመራርና ሠራተኞች የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎብኝተዋል።

የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ሚኪያስ ለገሰ በተባለ ወጣት ነው ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የተመሰረተው።

ማዕከሉ አሁን ላይ ከ180 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የአዕምሮ ሕሙማን ናቸው።

ማዕከሉ አረጋዊያን፣ ህፃናት፣ ሴቶች እና በአስቸጋሪ የጎዳና ህይወት ውስጥ የነበሩ ሰዎችን አሰባስቦ ምግብ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ያደርጋል።

ድርጅቱ የራሱ የሆነ ገቢ የሌለውና በሕብረተሰቡ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ሲሆን እስካሁን ወደ ማዕከሉ መጥተው ሕክምና የተደረገላቸው 34 ሰዎች ድነው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞችም ይህንኑ ሰብአዊ ተግባር እያከናወነ ያለውን ማዕከል ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ የኋላሸት አስፋው ማዕከሉ ሕሙማንን የሚደግፈው ከሕብረተሰቡ በሚያገኘው እገዛ በመሆኑ የሁሉንም ድጋፍ እንሻለን ብለዋል።

በተለይ ወደ እንጦጦ ፓርክ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን በዚያው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች ዛሬ ባደረጉት ጉብኝት መደሰታቸውን ገልጸው፤ የሕሙማን መርጃ ማዕከሉን በየጊዜው መጥተው እንዲጎበኙና ለሕሙማኑም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢዜአ የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንዲራድ፤ የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም