የደቡብ ክልል የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት እቅድ በውጤታማነት ቀጥሏል- የክልሉ ግብርና ቢሮ

285

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ከልል የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት እቅድ በውጤታማነት የቀጠለ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በ2014/15 የምርት ዘመን በክልሉ ተግባራዊ በተደረገው የ30፣ 40 እና የ30 የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት ከተቀመጠው እቅድ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑ ችግኞች መተከላቸውን አስታውቋል።

በፕሮጀክቱ በሶስት ዓመት ውስጥ አንድ ቤተሰብ እንደ የቅደም ተከተላቸው 30፣ 40 እና 30 በድምሩ 100 ፍራፍሬ ችግኞችን ለማስተከል ያለመ ነው።

May be an image of grass

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ 100 የፍራፍሬ ተክሎችን አልምቶ እንዲጠቀም ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ፕሮጀክቱ ባለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በክልሉ እንደ የአካባቢው ስነምሕዳር ተለይቶ ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በሁሉም የመንግስትና የእምነት ተቋማት አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲለማና ቢያንስ ከ100 እስከ 10 ሺህ የፍራፍሬ ዛፍ እንዲኖር የማድረግ ግብ መያዙንም እንዲሁ።

በከተሞችም የፍራፍሬ ዛፎች እንዲተከሉ እየተደረገ ሲሆን እየተካሔደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ከዚህ አንጻር የተቃኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍራፍሬ ዛፎች ባሻገር በአትክልትና ስራ ስር ልማት የክልሉን እምቅ አቅም በማልማት የምግብ ዋስትናን ጥያቄ የመመለስ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በተያዘው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 43 ሚሊዮኑ የፍሬፍሬ፣ 200 ሚሊዮኑ ደግሞ የእንስሳት መኖ መሆናቸው ተገልጿል።

በከተማ ግብርናም እንዲሁ ’አምስት፤ በአምስት’ በተሰኘው ፕሮጀክት አንድ ቤተሰብ በትንሹ አምስት አይነት የጓሮ አትክልትና ከሶስት እስከ ሰባት የሚደርስ ፍራፍሬ ዛፍ አልምቶ እንዲጠቀም የማድረግ ንቅናቄ ተቀርጿል።

በዚህ ፕሮጀክትም በህብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃት የተፈጠረበትና ተስፋ ሰጭ ለውጦች የተስተዋሉበት መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ዓመት ምርታማነትን ለማሳደግ ባለሀብቱን የማሳተፍ፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀምና የማቅረብ፣ የሜካናይዜሸን እርሻን ማስፋፋትና ክላስተርን የመጠቀም ስራ በትኩረት የሚኬድባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2014/15 የምርት ዘመን ክልሉ በ780 ሺህ ሄክታር መሬት በአምስት የሰብል አይነቶች ለመሸፍን ያቀደ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥ 75 በመቶ በኩታ ገጠም እንዲሁም 35 በመቶ በሜካናይዜሽን ይታረሳል ብለዋል።

ክልሉ ለቀጣይ የምርት ዘመን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ያቀርባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም