ከ487 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ግዥ አዋጅን ያልተከተለ ግዥ ተፈጽሟል

66
በአዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የግዥ አዋጅ  ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ከ487 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ፈጽመው መገኘታቸው ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥና ንብረት ኦዲት ዙሪያ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ በመከረበት ወቅት ነው፡፡ በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው የግዥ ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ ታደሰ እንደገለጹት ተቋማት የመንግስት የግዥ አዋጅ ሳይከበር ከ487 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ፈጽመዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ አመራሮች በበኩላቸው በተቋማቱ፣ እንደ ሀገር በሚከሰቱ ችግሮችና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች የኦዲት ጉድለቱ እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በኤጀንሲው የግዥ ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ ታደሰ  በተቋማቱ ግዥ በእቅድ ያለመፈጸም፣ ደንብና መመሪያ  ያለማክበር ችግር በዋነኛነት መስተዋሉን ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ወልዲያ ዩኒቨርስቲ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ መቱ ዩኒቨርስቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ እያንዳንዳቸው ከ21 እስከ 61 ሚሊዮን ብር  የግዥ አዋጁን ሳይከተሉ ግዥ ፈጽመው የተገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርስቲዎቹ አመራሮች በበኩላቸው በ2010 በጀት አመት ተፈጥሮ የነበረው ሀገራዊ ያለመረጋጋትና ከአቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች ምክንያት ከመመሪያ ውጪ ግዥዎችን እንዲፈጽሙ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የማዕቀፍ ግዥ መጓተት፣ ለሚከተሰቱ ድንገተኛ ችግሮች የሚወጡ ወጪዎችና ለትምህርቱ አገልግሎት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ለማሟላት በሚደረገው ጥረትም የኦዲት ግኝቱ መፈጠሩንም በምክንያት አንስተዋል፡፡ ስለሆነም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚቀመጠው የኦዲት መመሪያ መሻሻልና በልዩ ሁኔታ መዘጋጀትም እንዳለበት አመራሮቹ አጽእኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ የሚቀርቡ የኦዲት ግኝት ሪፖርቶችም የተፈጸሙ አስገዳጅ ሁኔታዎችን እንዲሁም የተሰሩ ስራዎችን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የመንግሰት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው ተቋማቱ በእቅድ እና በመርሃ ግብር መመራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በተቋማቱ አብዛኛው የሚፈጠሩ ክፍተቶችም በእቅድና በመርህ ካለመመራት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ እየተሻሻለ በመሆኑ የተለየ የማያስኬዳቸው መመሪያ ካለ እንዲሁም የተሰጡትም ግብዓቶች ተወስደው መፍትሔ እንደሚሰጣቸውም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም