ኢትዮጵያ ከፊቷ ለሚጠብቃት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስና ኦሊምፒክ ውድድር ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል -አቶ አገኘሁ ተሻገር

116

ነሐሴ 7 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከፊቷ ለሚጠብቋት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የሽልማትና እውቅና መርሐግብር ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ተካሄዷል።

በመርሐግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒሰትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሰት ባለስልጣናትና የስፖርቱ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት ”ኢትዮጵያና አትሌቲክስ ተነጣጥለው የማይታዩ አብረው የተገመዱ መለያዎቻችን ናቸው” ብለዋል።

ከእ.አ.አ 1960ዎቹ ሻምበል አበበ በቂላ በሮም በባዶ እግሩ ሮጦ ካስመዘገበው ውጤት አንስቶ ከ60 ዓመት በላይ አትሌቲክስ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ መድረኮች ሲያስጠራ መቆየቱንና አሁንም እያስጠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ድል ያስለመዱን አትሌቶቻችን በኮሎምቢያ ካሊ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደማቅ ውጤት አምጥተዋል ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው።

“የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቲክሱን በሚገባ በመምራት ያስገኘው ውጤት ሊደነቅ የሚገባው ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ ክስተቶች እያለፈች በምትገኝበት ወቅት አትሌቶች ሐዘኗንና ጭንቀቷን ለተወሰነ ጊዜ ቢሆን በማስረሳት አንገቷን ቀና በማድረጋቸው ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል በማለትም አመልክተዋል።

”እንደ አትሌቶቻችን ሁሉም በየተሰማራበት መስክ ጠንክሮ ከሰራና በአንድነት ከቆመ ተራራውና ገደሉ ሜዳ ይሆናል” ብለዋል አቶ አገኘሁ።

ኢትዮጵያ ከፊቷ ለሚጠብቋት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአትሌቲክስ ስልጠና ማዕከላትን ማጠናከር፣ተተኪ አትሌቶችን መመልመልና ከምንም በላይ የቡድን መንፈስን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ተከታታይነትና ቀጣይነት እንዲኖራቸው አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በልዩ ትኩረት መስራት አለበት ብለዋል።

ለዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚኖረው ዝግጅት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ አገኘሁ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ፣5 የብር እና 1 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪካና ጃማይካን ተከትላ ሶስተኛ ደረጃ መውጣቷ ይታወሳል።

በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ አትሌቶች ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም