የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሕጋዊ መብቷን ያረጋገጠችበት ነው-የሕግ ምሁራን

176

ጎንደር ነሐሴ 6/2014(ኢዜአ) የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ተርባይን የኤሌትሪክ ሃይል ለማመንጨት መብቃቱ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ህጋዊ መብቷን ያረጋገጠችበት ነው ሱሉ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁራን አመለከቱ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ መኳንንት ዱቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ እውን መሆን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ከመጠቀም የሚያግዳት ማንም ሃይል ሊኖር እንደማይችል ማሳያ ነው፡፡

“የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ በራሷዋ አቅም ማንኛውንም የልማት ስራዎች ማሳካት እንደምትችል ታላቅ ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከአለም አቀፍ የውሃ ህጎች አኳያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የተፋሰሱን ሀገሮች በማይጎዳ መልኩ በፍትሃዊነት የመጠቀም መርህን ኢትዮጵያ እየተገበረች መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን የሚከለክል አለም አቀፍ ህግ እንደሌለ ያስረዱቱ የህግ ምሁሩ “ከኤሌትሪክ ሃይል ባሻገር ለመስኖ ጭምር በመጠቀም ድህነትን መቅረፍ ይገባል”ሲሉ አመልክተዋል።

የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ወንዙን በጋራ ለመጠቀምና ለማደግ የሚያስችላቸውን የትብብር መንፈስ ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ጠቁመው፤ “ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ማደግን ምርጫቸው ማድረግ አለባቸው” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

”ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ የምትጠቀመው ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የራሷን ጥቅም ለማረጋጋጥና የሌሎችንም መብት በማክበር ጭምር ነው” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ስለሺ ዋለልኝ ናቸው፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን በህጋዊ መንገድ መቀጠም የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት መቀየር መቻል በመሆኑ ሀብታቸውን መጠቀም ላልቻሉ ደሃ ሀገሮች ኢትዮጵያ ታሪካዊ ምሳሌ መሆኑዋን አስረድተዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን በትናንትናው እለት ሀይል ማመንጨት መጀመሩ መበሰሩ ይታወሳል፡፡