በአገሪቱ የሥራ ገበያ ውስጥ ጊዜውን የዋጁ የፖሊሲ አማራጮች አለመተግበርና የቅንጅት ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ጉባዔ ሊካሄድ ነው

1562

ነሐሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአገሪቱ የሥራ ገበያ ውስጥ ጊዜውን የዋጁ የፖሊሲ አማራጮች አለመተግበርና የቅንጅት ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ጉባዔ ሊካሄድ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሁለተኛው ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ “ዘላቂ ሥራ ለብሩህ ነገ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ገልጿል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ጉባዔውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም በአገሪቱ የሥራ ገበያ ውስጥ ጊዜውን የዋጁ የፖሊሲ አማራጮች አለመተግበርና በሥራ ገበያው ውስጥ ባሉ ተዋናዮች መካከል የቅንጅት አሰራር አለመኖር ለዘርፉ ተግዳሮቶች ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በ2012 ዓ.ም ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ ማካሔድ የተጀመረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ የሚካሄደው ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ፤በሥራ ገበያው ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ የፖሊሲ ሃሳቦች ይነሱበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ጉባዔው መካሄዱ በአገሪቱ የሥራ ገበያ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ውይይት እንዲያደርጉ፣ የዘርፉን ችግሮች እንዲለዩ እና የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

አሰሪዎች የሚፈልጉትን የሥራ ክህሎት የሚገልጹበት፣ሥራ አጦች ደግሞ ሥራ በሚፈልጉበት ወቅት የሚገጥሟቸውን ውጣ-ውረዶች የሚያነሱበት እንደሆነም አስረድተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በዘርፉ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን መዛነፍ ለማጣጣም እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን የሚያቀርብበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በዚሁ የምክክር መድረክ ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጣቸው የሥራ መስኮችን የማዘመንና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ተግባር ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ሦስት ምርጥ የንግድ ሥራ ሃሳብ ባለቤቶች ተለይተው ለንግድ ሥራቸው መጀመሪያ የሚሆን የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም ዘርፉን የሚመለከቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን በ2013 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የዘርፉ ተዋናዮች ሽልማትና እውቅና እንደሚሰጥም እንዲሁ።

በውይይቱ ከትምህርት ሥልጠና ተቋማት፣ከአሰሪዎች፣ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ሥራና ሠራተኛ አገናኞች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ጉባዔው ነሐሴ 9 እና 10 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን እና ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።