እናንተ ኢትዮጵያውያን በልታችሁ ሳትጠግቡ ነገ ያልፍልናል ብላችሁ ለግድቡ ድጋፍ ያደረጋቹ ልትመሰገኑ ይገባል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

76

ነሐሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለህዳሴው ግድብ ድጋፍና ርብርብ ያደረጉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊመሰገኑ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት የማጠናቀቂያ ማብሰሪያ መርሃ ግብር ላይ እንደተናገሩት ግድቡ የኢትዮጵያውያን እንችላለን የሚለውን መንፈስ የሚያሳይ ነው ፤ ግድቡ የአሸናፊዋ ኢትዮጵያ ገጽታ ነው።

አባይ ላይ ግድብ መስራት ለትውልዶች እንደ ሩቅ ህልም የሚታይ እንደነበርም አንስተዋል።

“እኛ ባንችል ትውልድ ይሰራዋል ብለው የተናገሩ መሪ ነበሩን ቀጥሎ ድፍረቱን ወደፊት ገፍተው ለዚህ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ያስቀመጡ መሪ ነበሩን ይህንን ስራ ያስቀጠሉ መሪም ነበሩን ቀዝቅዞና ተቋርጦ የነበረውን ስራ ያስቀጠሉም” ሲሉም ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ከረሃብ፣ከችግር ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ አለብን ብለው የተነሱ መኖራቸውንም አንስተዋል።

“ይህንን ስራ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ አሁን እንደምናየው ግድቡ ሀይል ማመንጨት ድረስ እንዲደርስ ያደረጉ ከአንድም ሁለተኛው ተርባይን እንዲጀምር ሶስተኛው ሙሌት እንዲካሄድ ተስፋችን እውን እንዲሆን ያደረጉ መሪ ደግሞ አይተናል” ብለዋል ።

የግድቡን ግንባታ አሁን በህይወት የሌሉ አመራሮች እና እንደነ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ያሉ አመራሮች መርተውታል የውጭ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም