ባለፉት አራት ዙሮች ከ150 ሺህ በላይ ችግኞች በአካል ጉዳተኞች ተተክለዋል

119

ነሐሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት አራት የችግኝ ተከላ ዙሮች ከ150 ሺህ በላይ ችግኞች በአካል ጉዳተኞች መተከላቸውን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌዴሬሽኑ በ16 ከተሞች ሲያካሄድ የቆየውን አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማጠቃለያ መርሃ- ግብር አካሂዷል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ እንደገለጹት፤ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡

በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአካል ጉዳተኞች ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።

የተተከሉ ችግኞችም በተደረገላቸው የእንክብካቤና የጥበቃ ሥራ ከ70 በመቶ በላይ  ማጽደቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን እንክብካቤ በማድረግ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ጽድቀት እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል፡፡

በዛሬው እለትም በ16 ከተሞች 50 ሺህ ችግኞችን በመትከል አራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርሃ-ግብር አካሂደዋል፡፡

በዚህ መርሃ-ግብርም 17 ሺህ አካል ጉዳተኞች እየተሳተፉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ በበኩላቸው፤ “እኛም እንችላለን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው ችግኝ ተከላ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች ባለፉት ሦስት ዓመታት ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን እንዲጸድቅ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነውም ብለዋል፡፡

ባለፉት ሦስት የችግኝ ተከላ ዙሮች የተለያዩ ቢሮዎች ስኬታማ ካደረጓቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ውስጥ  የአካል ጉዳተኞች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩ ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም