ትምህርት ቤቶችን ለመማሪያ ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡም ሳቢና ማራኪ ማድረግ ይገባል - ትምህርት ሚኒስትሩ

129

ወልዲያ ነሐሴ 6/ 2014 (ኢዜአ) ትምህርት ቤቶችን ለመማሪያ ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡም ሳቢና ማራኪ አድርጎ መገንባት ይጠበቃል ሲሉ የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰሜን ወሎ ዞን በመርሳ ከተማ ለሚገነባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት ህዝባዊና አገራዊ ጥላቻውን ከሚገልጽባቸው ተቋማት ዋናዎቹ ትምህርት ቤቶች ናቸው።

ወራሪ ቡድኑ ለአገር ተስፋ የሆነውን ወጣት ህልም ለማምከን አልሞ በመንቀሳቀስ በወራረ በገባባቸው አካባቢዎች 1ሺህ 300 ትምህርት ቤቶች ላይ ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።

አካባቢዎቹ ከአሸባሪው ነጻ ሲወጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የትምህርት ቤቶች መውደም ችግር ፈጣሪ ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ትምህርት ቤቶችን በፊት ከነበሩበት በተሻለ ለመገንባት ከአጋር አካላት፣ ባለሃብቶችና ህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

"ትምህርት ቤቶችን ለመማሪያ ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡም ሳቢና ማራኪ አድርጎ መገንባት ይጠበቃል"  ያሉት  ፕሮፌሰር ብርሃኑ  በአሸባሪው የወደሙ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በተሻለ እንደሚገነቡ አስታውቀዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ ከተማ የሚገኘውን የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰዎች ለሰዎች ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር መልሶ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን አመልክተዋል።

"ትምህርት ቤቱ ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ባሻገር ስለአካባቢያቸውና አገራቸው ነባራዊ ሁኔታ እየተገነዘቡ ለፍሬ የሚበቁበት ሁኔታ ይፈጠራል" ብለዋል።

ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ መምህራን፣ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና የፖለቲካ አመራሩ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው አስማሜ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ባደረሰው ውድመት በትምህርት ቤቶች የፕላዝማ፣ ቤተ-ሙከራና ቤተ- መጻህፍት ችግር መፈጠሩን አመልክተዋል።

ችግሩ በአዲሱ ዓመትም ቀጥሎ ለትምህርት ጥራት ችግር እንዳይሆን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማቋቋም በኩል ትምህርት ሚንስቴርና ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ቶሎሳ እንዳሉት ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ከ16 ማሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዟል።

የአካባቢው መስተዳድር የግንባታ ቦታውን ከ3ኛ ወገን ነጻ በማድረግ ከወዲሁ እንዲሰራ ጠቁመው ድርጅታቸው ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

የመልካ-ጨፌ ትምህርት ቤት ርእሰ መምር አቶ በላይ አስፋው በበኩላቸው "የግንባታ ቦታውን ባጭር ጊዜ ውስጥ ከሶስተኛ ወገን በፍጥነት ነጻ አድርገን እናስረክባለን" ብለዋል።

የአካባቢው የአገር ሽማግሌ አቶ በላይ ሞላ  "ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ስኬታማነት ማህበረሰቡ የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም