በአማራ ክልል በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ተተከለ

96

ባህር ዳር ነሐሴ 5/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ህብረተሰቡን በማስተባበር 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛንን ለማስተካከል ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር  የአካባቢን ስነ-ምህዳር መሰረት በማድረግ ከተዘጋጀው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ እስካሁን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን  ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።  

በተከላው የእቅዱን 91 ነጥብ 3 በመቶ ማከናወን እንደተቻለ ጠቁመው፣  ከተተከለው ችግኝ ውስጥ ከ263 ሚሊዮን የሚበልጠው በአንድ ጀምበር በተካሄደ መርሃ ግብር የተተከለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ችግኞቹ ከ171 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የተጎዳና የተራቆተ መሬት ላይ መተከላቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከተተከሉት ችግኝ ውስጥ ከ10 ሚሊዮን በላዮቹ  ማንጎና አቦካዶን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው  የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በችግኝ ተከላው ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መሳተፉን የገለጹት ዳይሬክተሩ ቀድሞ ዝናብ በበቂ ሁኔታ መጣል በጀመረበት በምዕራብ አማራ አካባቢ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሀግብር መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የዝናብ ስርጭት ችግር በነበረባቸው በዋግህምራና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ወሎ ሁለት ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላም በያዝነው ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

ዳይሬክተሩ አክለው "ቢሮው አንድም ችግኝ ባለቤት ሳይኖረው መተከል የለበትም የሚል መርህን ይዞ የችግኝ ተከላውን ማካሄድ በመጀመሩ ህብረተሰቡ የሚተክላቸውን  ችግኞች በቀላሉ እንዲንከባከብ ለማድረግ ያስችለዋል" ብለዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ አማራ አካባቢ የዝናቡ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የተተከሉ ችግኞችን ህብረተሰቡ የመንከባከብ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት በተካሄደው 3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከለው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ 77 በመቶው መፅደቁ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም