የህዝብና የመንግስት ተቀናጅቶ መስራት አሸባሪውን ሸኔ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እያደረገ ነው - ብርጋዴር ጀኔራል ከበደ ገላው

109

ግምቢ፣ ነሐሴ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህዝብና የመንግስት ተቀናጅቶ መስራት በምዕራብ ወለጋ ዞን አሸባሪውን ሸኔ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እያደረገ ነው ሲሉ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዞኑ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ከበደ ገላው ገለጹ።

ብርጋዴር ጀኔራሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተለይ ባለፈው አንድ ወር በጸጥታ ሃይሉና በህብረተሰቡ የተቀናጀ ጥረት ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በአሸባሪው ቡድን የተዘረፉ የህብረተሰቡ ንብረቶች እየተመለሱ ነው፡፡

በዚህም በዞኑ በቦጂ ጨቆርሳና ግምቢ አካባቢዎች ተዘርፈው የነበሩ 105 የቀንድ ከብቶችና 10 በጎች ለየባለቤቶቹ መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በግምቢ ወረዳ ሶጌ ከተባለው አካባቢ በቡድኑ የተዘረፈ ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ በቆሎ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ሌላ 10 ሞተር ብስክሌት፣ 200 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ 108 የዲሽቃ ጥይቶች፣ ድምጽ አልባ የጦር መሳሪያዎችና አንድ ጀኔሬተር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብራርተዋል።

በተደረገው ኦፕሬሽን 20 የአሸባሪው ሸኔ አባላት በሰላም እጃቸውን ሲሰጡ፤ ለማምለጥ በሞከሩት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ተስፋ በመቁረጥ ላይ መሆኑን የተናገሩት ብርጋዴር ጀኔራሉ፤ በመንግስት የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅቱ ያለምንም ስጋት በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የየዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ ውስጥ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስታውቀው፤ የተጀመረው ቡድኑን የመደምሰስና ሰላም የማስከበር ተልዕኮ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የግምቢ ከተማ ነዋሪ አቶ ደርባቸው ሆርዶፋ በሰጡት አስተያየት፤ በአሁኑ ወቅት በጸጥታ ሃይሉና በህዝቡ ቅንጅት በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፋችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ የግምቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኩምሳ ቦጋለ ናቸው።

ቡድኑ እስከሚጠፋ የጸጥታ ሃይሉን በመደገፍ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚያበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል አቶ ኩምሳ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም