ኢትዮጵያና ህንድ በትምህርት ዘርፍ የፈጠሩት ትስስር ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጎልበት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ይገኛል -አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ

226

ነሃሴ 4/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያና ህንድ በትምህርት ዘርፍ የፈጠሩት ትስስር ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጎልበት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ገለጹ።

ኢንስቲትዩቱ ከአራት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙም ነው የተገለጸው፡፡

የህንድ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (ሩርኪ) 175ኛ የምስረታ በዓሉን ከቀድሞ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎቹ ጋር በአዲስ አበባ አክብሯል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በዚሁ ወቅት፤ በርካታ የህንድ ምሁራን በኢትዮጵያ በማስተማር ስራ ላይ በመሳተፍ የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን  ገልጸዋል።

ይህም በሁለቱ አገራት ያለውን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና መጫዎቱን  ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም 1 ሺህ 500 ያህል ህንዳዊያን ፕሮፌሰሮችና መምህራን ከ40 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምርና ማስተማር ስራ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

“ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ትምህርት አሁንም አስፈላጊ መሳሪያ ነው” ያሉት አምባሳደሩ፤ በህንድ ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጎልበት ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውንም አንስተዋል።

የህንድ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማኖራነጃን ፓሪዳ፤ ኢንስቲትዩቱ ከአራት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲዎች ጋር በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በትብብር ለመስራት ስምምነት ማድረጉን  ገልጸዋል።

በቀጣይም ከሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በትብብር ለመስራት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተማሪዎችን በማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የቀድሞ የኢንስቲቲዩቱ ተማሪዎች ገልጸዋል

በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ከሚባሉ የቴክኖሎጂ ምርምር ተቋማት መካከል የሚጠቀሰው የህንድ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (ሩርኪ) የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ለመደገፍ ከወለጋ፣ ሐሮማያ፣ ጎንደር እና አምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ኢንስቲትዩት ከ57 የዓለም አገራት የተውጣጡ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም