በሶማሌ ክልል ከ159 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

95

ጅግጅጋ፤ ነሐሴ 4/2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ከ159 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በክልሉ የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል በሚቻልበት ዙሪያ ከስራ ፈጣሪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በጅግጅጋ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ምክትል  ርዕሰ መስተዳድር የስራ እድል ፈጠራ አማካሪ አቶ ከማል ሼህ መሀመድ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራባቸው ካሉት እርሻ፣ እንስሳት እርባታ፣ የቤትና ቢሮ እቃዎች ማምረቻ፣ ግንባታና አገልግሎት ዘርፎች ይገኙበታል።

በዘርፎቹም ከ159 ሺህ  ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር  ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በየወረዳው ያሉ ስራ አጥ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ስራ ለማሰማራት የመንግስት ሀብት ውስን በመሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ ባለሀብቶችና ነባር ኢንተርፕራይዞች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ እንዲህ ዓይነት የጋራ መድረክ ዋሳኝ ነውም ብለዋል።

የክልሉ የክህሎትና ስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሂቦ አህመድ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  ከ102ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስታውሰዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

በክልሉ ያሉ ስራዎች ከፈላጊዎች ጋር ለማስተሳሰር እንቅፋት ከሆኑትም የህብረተሰቡ የስራ ባህል በሚፈለገው መልኩ አለማደግ፣ አነስተኛና መካከለኛ የሙያ ስራዎች ላይ ለመሰማራት በወጣቶች ዘንድ የሚታየው የግንዛቤ እጥረትና የአመለካከት ችግር፣ የመስሪያ ቦታና የሼድ አቅርቦት አለመኖርን ጠቅሰዋል።

ለእነዚህ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥና ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማነሳሳት መድረኩ መዘጋጀቱ ተመልክቷል።

በመድረኩም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፣ስራ ፈጣሪ ተቋማት ፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች ፣ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ፣የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀት አባላትና አስተባባሪዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም