በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወር ከመካከለኛ ግብር ከፋዮች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል- ገቢዎች ሚኒስቴር

109

ነሃሴ 4/2014/ኢዜአ/ የገቢዎች ሚኒስቴር በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወር ከመካከለኛ ግብር ከፋዮች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ፍቃደ ለኢዜአ እንደተናገሩት በ2015 በጀት ዓመት ከመካከለኛ ግብር ከፋዮች በአጠቃላይ 33 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

ከዚህም ወስጥ  2 ነጥብ 4 ቢሊዮኑን በሐምሌ ወር ለማሳካት እቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በሐምሌ ወር ብቻ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አፈጻጸሙ ከእቅድ በላይ መሆኑንና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ ከ47 በመቶ በላይ ጭማሪ እንዳለውም ነው የጠቆሙት፡፡

ይህም በቀጣይ የበጀት ዓመቱን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

አጠቃላይ በገቢ አሰባሰቡ ብቻ ሳይሆን የክፍያ ስርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ ረገድም የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ በ2014 በጀት ዓመት ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት እንዲያከናውኑ መደረጉንም ገልጸዋል።

የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ግብርን በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ስራቸውን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎች መከናወናቸውም እንዲሁ፡፡

የስነ-ምግባር ጉድለት የተገኘባቸው የቅርንጫፉ ሰራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከመካከለኛ ግብር ከፋዮች 22 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም