በኢትዮጵያ የሚኖሩ ከ750ሺህ በላይ ስደተኞችን ለመደገፍ ተጨማሪ 73 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

174

ነሐሴ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚኖሩ ከ750 ሺህ በላይ ስደተኞችን ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለመመገብ ተጨማሪ 73 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣የአለም የምግብ ፕሮግራም እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታወቁ።

የአለም ምግብ ፕሮግራም ለስደተኞች የያዘው የምግብ ክምችት በጥቅምት ወር የሚያልቅ ሲሆን ይህም ስደተኞችን ለምግብ እና ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት እንዲሁም ለበሽታ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ሶስቱ ተቋማት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ክላውዴ ጂቢዳር እንዳሉት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ስደተኞችን ለመመገብ ቢያንስ 73 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን ከተለያዩ አጋር አካላት የሚገኘው እርዳታ እየቀነሰ የሚሄድ ከሆነ ግን ስደተኞቹ ለኑሮ ምቹ ወዳልሆነ የትውልድ ቦታቸው ለመመለስ ይገደዳሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የስደተኞች የምግብ ክምችት ለመጀመሪያ ግዜ በ16 በመቶ ያህል መቀነስ ያሳየው እ.አ.አ በህዳር ወር 2015 ሲሆን በመቀጠልም እ.አ.አ በ2021 በ40 በመቶ ያህል ቀንሷል። አሁን ያለው የምግብ ክምችት መጠን 50 በመቶ ያህል ብቻ መሆኑም ተመላክቷል።

የተባባሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ማርጋሬት አቴኖ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች የምግብ እጥረት እንዳያጋጥማቸው ተጨማሪ እርዳታ ከለጋሾች ያስፈልጋል ብለዋል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በስደተኞች እና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ያለውን ሰላማዊ የሆነ አብሮ የመኖር ልምድ ሊፈትነው እንደሚችልም ስጋታቸውን አጋርተዋል።

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተስፋዬ ጎበዛይ እንዳሉት ኢትዮጵያ የተሻለ የስደተኞች ፖሊሲ ያላት እና ስደተኞችን ለማገዝ ቁርጠኛ የሆነች ሀገር ስትሆን ከአለም አቀፍ ለጋሾች ካጋጠመው የገንዘብ እጥረት ባሻገር ስደተኞች በቀጣይ ራሳቸውን በዘላቂነት እንዲችሉ ለማድረግ እየታገለች ትገኛለች።

አሁን እያጋጠመ ያለው የምግብ እጥረት በዚህ ከቀጠለ በየአካባቢዎች ካለው የምግብ እጥረት ጋር ተዳምሮ ግጭት እንዳይፈጥር ስጋት አለን ብለዋል።

በተጨማሪም ችግሩ በአፋጣኝ ካልተፈታ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለችውን ፈጣን እድገት ወደ ኋላ በመመለስ ስደተኞች ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት እና ከህብረተሰቡ ጋር አብሮ የመኖር ሂደት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ይከተዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ 85 በመቶ የሚሆኑ ስደተኞች ከአለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም ክምችት ተጠቃሚ የሚሆኑ ናቸው።

ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞችን እና የፖለቲካ ጥገኞችን እያስተናገደች ትገኛለች፤በስደት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ስደተኞች መካከል የደቡብ ሱዳን፣ኤርትራ እና የሱዳን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን 750 ሺህ የሚሆኑት ስደተኞች ሙሉ ለሙሉ የምግብ እርዳታ የሚደረግላቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም