በክልል ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል - ኡሞድ ኡጁሉ

107

ጋምቤላ፤ ነሐሴ 3/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ከዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተዋወቅ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ አስታወቁ።

በክልሉ ሁለት  ወረዳዎች ከ71 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ  የተለያዩ የግብርና ምርት ማሳደጊያና ጥራት ማስጠበቂያ ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮክቶችን በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉ ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በግብርና ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እንደ ሀገር ሰንዴን ጨምሮ በውጪ ምንዛሬ ሲገቡ የነበሩ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት  የተያዘውን ግብ እንዲሳካ  የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ  ለምረቃ የበቁት የመስኖ ፕሮጀክቶች በተለይም እንደ ሀገር የተጀመረውን የቆላ ስንዴ ልማት ለማስፋት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በተለይም  በስንዴ ልማት የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄን ጨምሮ የሩዝ፣ የቅባት እህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ   ለኢኮኖሚ  አስተዋጽኦ ከማሳደግ አኳያ  የፕሮጀክቶቹ ሚና  ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአርሶ አደሩን ክህሎት ለመጨመርና የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተገነቡት ዘመናዊ የአርሶ ማሰልጠኛ ማዕከልና የማር ማቀነባበሪያ ማዕከል የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ረገድ የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው፤ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ዛሬ  ከ71 ሚሊዮን በሚበልጥ ወጪ የተገነቡት የግብርና ምርት ማሳደጊና የምርት ጥራት ማስጠቢያ ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በጋምቤላና አቦቦ ወረዳዎች ዛሬ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለት አነስተኛ የመስኖ ፣የማር ምርት ማቀነባሪያ፣ የሰብል ግብይትና ዘመናዊ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት እንደሚገኙበት ኃላፊው ጠቅሰዋል።

አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ከ202 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ800 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደረጉም አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቶቹ ወጪ በዘላቂ የልማት ግቦች፣ በምዕራፍ ሁለት የግብርና እድገት ፕሮግራምና በዓለም የምግብ ፕሮግራም የተሸፈነ መሆኑም አቶ አጃክ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም