የግብርና ምርታማነትን የሚቀንሱ ተባዮች፣ በሽታና አረምን ለመከላከል የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እየተደረገ ነው

105

ነሀሴ 3/2014 (ኢዜአ) የግብርና ምርታማነትን የሚቀንሱ ተባዮች፣ በሽታና አረምን ለመከላከል የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ ላይ የሚታዩ የተባይ፣ የበሽታና የአረም ጉዳቶችና መከላከያ መንገዶች ላይ ምክክር ተካሒዷል።

የግብርና ሚኒስቴር ከዎርልድ ቬጄተብል ሴንተር፣ ከአይካ ፋውንዴሽን፣ ከዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ነው ምክክሩን ያካሔደው ።

በመድረኩም በሆርቲካልቸር ምርት ላይ ተባይ፣ አረምና በሽታዎች በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ  እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች ተነስተዋል።

በአዝርዕት ላይ የሚመጡ በሽታዎች ፣ተባዮችንና አረሞችን ለመከላከል በቅድሚያ የዘር አይነቶችና የአፈሩን ሁኔታ ማወቅ እንደሚያስፈልግ የመድረኩ ፅሁፍ አቅራቢ ዶክተር ተስፋዬ አለሙ ገልጸዋል።

“የዘሩንና የአፈሩን ሁኔታ በመለየት የመከላከል ስራው ካልተሰራ ደግሞ ከ35 እስከ 42 በመቶ የምርት መቀነስን ሊያስከትል ይችላል” ነው ያሉት ።

በመሆኑም ዘመናዊና ጊዜው ያፈራቸውን ስነ ሕይወታዊ መንገዶች በመጠቀም ችግሩን መቅረፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ተባዮችን በመከላከል ሂደት  በሀገር ውስጥ የሚገኙ አስቻይ ሁኔታዎችን በመጠቀም ችግሩን ለመከላከል  የሚወጣውን ወጪ ማስቀረት አለብን ያሉት ደግሞ የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ዋቅቶሌ ሶሪ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ችግሩን ለመከላከል  የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ በቤተ ሙከራና የሰው ሃይል ግንባታን በማሳደግ እንደ ሐገር ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግም በመጠቆም።

የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሠ መኮንን፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሂደት ውስጥ በርካታ ፈታኝ ጉዳዩች እንዳሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥም ዋነኞቹ በሰብል ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች፣ ተባዮችና አረሞች  ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እተደረገ መሆኑን አንስተው ባህላዊና ዘመናዊ መከላከያ መንገዶችን ያስተሳሰረ የተቀናጀ የተባይ መከላከያ መንገድ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን በዘላቂት ለመፍታት የሚያስችሉ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ መሻሻያ እየተደረጉ ሲሆን ተቋማትን የማደራጀት ስራ እየተካሔደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በግብርና ምርቶች ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ተባዮች፣ አረሞችና በሽታዎች ምክንያት በመቶ ቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ምርት እንደሚባክን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም