ከ121 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለወጭ ንግድ የሚውል አኩሪ አተር እየለማ ነው

136

ባህርዳር ነሃሴ 03/2014 በምዕራብ ጎንደር ዞን በተያዘው መኽር ወቅት ከ121 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለወጭ ንግድ የሚውል የአኩሪ አተር ልማት እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰብሉ እየለማ ያለው በ450 ባለሃብቶችና 40ሺህ በሚሆኑ አርሶአደሮች ነው።

በመተማ፣ ቋራና ምእራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ከለማው ከ121ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ ከ32 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በባለሃብቶችና ቀሪው በአርሶአደሮች ማሳ ላይ የለማ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በተያዘው መኽር ወቅት የአኩሪ አተር ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ 800 ኩንታል የሚጠጋ ምርጥ ዘርና ከ86 ሺህ ኩንታል በላይ የአካባቢ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል" ብለዋል።

በተጨማሪም 4ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የፋብሪካ ማዳበሪያ  ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

ባለሞያው እንዳሉት የአኩሪ አተር ልማቱ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግና  የምግብ ነክ ፋበሪካዎችን የግብአት ፍላጎት ለማሟላት የአየር ንብረታቸው ተስማሚ በሆኑ ወረዳዎች በኩታ ገጠም ማሳ ላይ ጭምር እየተካሄደ ነው ።

በሰብሉ ከለማው አጠቃላይ ማሳ ውስጥ  ከ70ሺህ ሄክታር በላዩ ኩታ ገጠም መሆኑን አመልክተዋል።

እየለማ ካለው አኩሪ አተር  ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያው አመላክተዋል፡፡

የመተማ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደመቀ መልካሙ በምርት ወቅቱ እየታየ ያለው የዝናብ መጠን መብዛት ከሰሊጥ ይልቅ ለአኩሪ አተር ምርታማነት የሚመች በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።

በአኩሪ አተር ዘር ከሸፈኑት አራት ሄክታር መሬት ላይ 90 ኩንታል የሚጠጋ ምርት በማግኘት ገቢያቸውን ለማሻሻል እንዳሰቡም ተናግረዋል።

በምርት ወቅቱ  ከ130 ሄክታር በላይ መሬት  ላይ አኩሪ አተር ዘርተው እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብት አቶ ጌትየ ገብሩ ናቸው ።

አሁን ላይ አረምንና ተባይን በአግባቡ እየተከላከሉ በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።

"ለልማቱ 100 ኩንታል ዘር ተጠቅሚያለሁ፣ ከ2ሺ 300 ኩንታል በላይ ምርት እጠብቃለሁ" ብለዋል ።

በዞኑ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ምርት ወቅት  በ60 ሺህ ሄክታር መሬት ከለማ አኩሪ አተር ከ1ሚሊዮን  ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም