በቡራዩና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች የመንግስትን እገዛ ጠየቁ

137
አዲስ አበባ መስከረም 6/2011 በአዲስ አበባ አቅራቢያ ቡራዩና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ። የዚህ ዓይነቱ ድርጊት በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸም መሆኑን የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን መፈናቀል እንዲገታ ጠይቀዋል። ተፈናቃዮቹ በተለያዩ ቦታዎች የተጠለሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ ወረዳ 6 ወጣት ማእከል ከሚገኙት አንዳንዶቹን የኢዜአ ሪፖርተር አነጋገራቸዋለች። አስተያየት ሰጪዎቹ እንደገለፁት ለመፈናቀል እየተዳረጉ ያሉት አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ በሚሉ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት ሳቢያ ነው። ከመፈናቀላቸውም ባሻገር ከመካከላቸው ህይወታቸውን ያጡና ለአካል ጉዳት የተዳረጉ መኖራቸውንም ገልጸዋል። ጨቅላ ህፃናት ፣ አራስ እናቶችና አረጋዊያን ጭምር የሚገኙባቸው ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በሽሮ ሜዳ አካባቢ ወረዳ 6 ወጣት ማእከል ተጠልለው የሚገኙ ቢሆንም በቂ መሰረታዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል። የፀጥታ አካላት በስፍራው በመገኘት ሁኔታውን እንዲያረጋጉ፤ የጠፉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን የማገናኘት ተግባር እንዲሰራ ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል። ከአስኮ ጫፍ አካባቢ የመጡት ወይዘሮ ሙሉ በንቴ ቤታቸውን በትነው መምጣታቸውን ተናግረው በአሁኑ ወቅት የሰው ህይወት ጭምር እጠፋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከቡራዩ ቄራ አካባቢ የመጡት ወይዘሮ አየለች ፋንቱ በበኩላቸው በማናውቀወ ሁኔታ ሜዳ ላይ አስቀርተውናል በአካባቢው በደረሰብን ትቃት ሊከላከልልን የሚችል ሰው አጥተናል ብለዋል፡፡ ከቡራዩ ከደስታ መንደር እንደመጡ የሚናገሩት ወይዘሮ ወርቅነሽ ደጎዬ በበኩላቸው ከምሽቱ ስድስት ሰአት ጠሩ ስላሴ ነፍሳችንን ይዘን ንብረታችን ተዘርፎ  ወጥተናል ምንም ነገር የቀረ ነገር የለም የእቁብ ብር ሁሉ የተሰበሰበ 15 ሺህ ብር የቤት እቃ የ60 የ70 ሺህ የሚገመት ከወደመ ወዲህ በቃ ነፍሳችንን ይዘን ዘመድ በመኖሩ ጠሩ ስላሴ ዘመድ ጋር መጥተን ነበር ያረፍነው ብለዋል። አቶ ይሳቅ ከበደ  ከቡራዩ ገፈርሳ አካባቢ እንደመጡ ተናግረው እኛ ምን እንደሆነ አናውቅም በየአመቱ ነው ይሄ ነገር የሚፈጠርብን አምናም ካቻምናም ነበር አሁንም ተከስቷል የአሁኑ ሃሙስ ነው የጀመረው ከየት እንደመጡ ሳይታወቅ እንደ ደራሽ ውሃ መጥተው ቤታችንን አፈረሱ ሰው ሞተ የመጡ እለት አራት ሰው ነው ገድለው የሄዱት ከዛ ለኦሮሚያ እና አሁን መንግስት ብቻ ንብረትም ከስሯል ችግር የለም ቤትም ችግር የለም ግን እዛ ያሉ ወገኖቻች ቢወጡልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ መኩሪያ ጉዶ ከቡራዩ ነው ተሰደው የመጡት ንብረቴ እንዳለ ተሰባብሮ ደጅ ቁጭ ብሏል ከልጅነቴ ጀምሮ እስከአዋቂነቴ የሰራሁትን ንብረቴን ጠቅላላ አወደሙብኝ ምን አይነት ተግባር ነው ይሄ የትረኛው አካል ነው እንደዚ የሚያደርገው ምን አደረኩኝ እኔ ፖለቲካ ውስጥ የለሁ ሸማ ሰርቼ ነው የምኖረው ምን አድርጌ ነው ልጆቼን እያሳደኩ ነው ያለሁት የአካባቢው ሰው ጋር ሰላም ነኝ ከነሱ ጋር አምስት ስድስት እድር ገብቼ ነው ያለሁት። ግን ምን አይነት ዱብዳ ነው የወረደብኝ እንደኔ የተመቱ ሰዎች መአት ህዝብ አለ ብለዋል። እኔ ከቤቴ ከወጣው ሶስተኛ ቀኔ ነው የሚለው አቶ ኤልያስ ጨንደሬ ከቡራዩ ተፈኛቅሎ ነው የመጣው ባለቤቴ የት እንዳለች ልጆቼ የት እንዳሉ እኔ የማውቀው ነገር የለም ስለዚህ ልጆቼ በረሃብ እየሞቱ ነው ብዙ ቤተሰቦቼም እየሞቱ ነው ስለዚህ እኔ መግቢያ መውጫ አጥቼ አሁን ብበላም ባልበላም እዚህ ተጠልያለሁ። ብላል፡፡ ተፈናቃዮችን ያስጠለለው የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት በበኩሉ ድርጊቱ ተደጋጋሚ በመሆኑ ኦሮሚያ ክልል ከከተማ መስተዳደሩ ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል ብሏል። የወረዳው የጥቃቅንና አነስተኛ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኃይለማሪያም አንጄሎ እንደገለጹት ድርጊቱ በሚፈጽሙ አካላት ላይ የተጠያቂነት አሰራሩን በማጠንከር የጸጥታ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። በተጨማሪም ተፈናቃዮችን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከወረዳው ነዋሪ ህብረተሰብ ጎን በመሆን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጥሪ አስተላልፈዋል። የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ እጅጉ ከሁለት ቀን በፊት ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ የተደራጀ የዘራፊ ቡድን በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። የኦሮሚያና ፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት በጋራ በመሆን ወንጀለኞችን የመያዝ ተግባር እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ70 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ችግር ፈጣሪዎችን የመያዝ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። እስካሁን ባለው መረጃ በአካባቢው በተፈጠረው ችግር 23 ሰዎች ሲሞቱ 886 ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም