ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ

156

ነሐሴ 3/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በትብብር ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የኦቪድ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ተናገሩ።

'ኩባንያው በኢትዮጵያ የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አዲስ ተስፋ መኖሩን በተግባር ማሳየት መቻሉንም ተናግረዋል።

የ"ኦቪድ" ግሩፕ የግንባታ ኩባንያ ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በ18 ወራት ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ገንብቶ አጠናቋል።

ኩባንያው እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2013 በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሚታየውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ መቋቋሙ ተገልጿል።

የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኩባንያው ከተመሰረተ ጀምሮ አማራጭ የግንባታ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የዘርፉ ተዋናዮች በትብብር መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ አገርና ሰፊ ሕዝብ ያላት እንደመሆኗ ሁሉም በትብብርና በቅንጅት ቢሰራ የበለጠ ውጤት ይገኛልም ነው ያሉት።

"ኦቪድ" ኩባንያም ይህንኑ በመረዳት በቀጣይ ከተለያዩ አጋሮች ጋር ትብብር እየፈጠረ የተሻለ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ግንባታዎች በተያዘላቸው ወጪና ጊዜ ሲጠናቀቁ እንደማይስተዋልም አንስተዋል።

"ኦቪድ" ኩባንያ ግን ወደ ግንባታው ዘርፍ ከተቀላቀለ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ተስፋ መኖሩን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

ለአብነትም የድርጅቱ እህት ኩባንያ "ኦቪድ" ሪል ስቴት 12 ወለል ያለው ሕንጻ በሦስት ወራት ሰርቶ ማጠናቀቅ መቻሉን አንስተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም 10 ወለል ያለው ሕንጻ በ69 ቀናት ገንብተው ማጠናቀቃቸውን አንስተው፤ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ መኖሪያ ቤት ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር የተሰራው የገርጂ ሳይት የመኖሪያ መንደር ሕንጻዎቹ ከ1 እስከ 10 ወለሎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መገንባታቸውን አንስተዋል።

በግንባታው ከተያዘው ጊዜ ውስጥ ስድስት ወራት የሚሆኑት የዝግጅት ሥራዎች የተሰሩባቸው እንደነበረም ገልጸዋል።

"ኦቪድ" በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታገዙ ብቻ ውጤታማ እንደማያደርግ በአግባቡ የተረዳ ኩባንያ መሆኑንም ሥራ አስፈጻሚው አንስተዋል።

ኩባንያቸው በከፕሮጀክቱ መሪዎች እስከ ሠራተኞች ድረስ በአገር ወዳድነት ስሜት በግንባታው ላይ የሚሳተፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይም የኩባንያው ሠራተኞች ፕሮጀክቶችን መገንባት አገር መገንባት መሆኑን እንዲረዱ ማስቻልና አስፈላጊውን ማበረታቻዎች እንደሚያገኙ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር በ2014 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች ከ70 በላይ ቤቶች ግንባታና እድሳት ላይ መሳተፉንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም