በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል- ፌዴሬሽኑ

107

ነሐሴ 3/2014 (ኢዜአ) በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ ከምክክር ኮሚሽኑና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ አባላቱና በሥሩ ያሉ ማህበራት  በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር ጠቃሚ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ ከተመሰረተ 25 ዓመታት ማስቆጠሩን አስታውሰው፤ የአገሪቷ ሕገ-መንግሥት በጸደቀበት ወቅት ፌዴሬሽኑ እውን ስላልነበር ተሳታፊ እንዳልነበሩ ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ ከተመሰረተ በኋላ ግን የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ መሆኑን ጠቅሰው፤ አካል ጉዳተኞችም የዚሁ ተሳትፎ አንድ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክሩ በባለሙያነትም ሆነ በሌላ አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፏቸው ይጠበቃል ብለዋል።

በኮሚሽኑ ስትራቴጂም የአካል ጉዳተኞች ተሳታፊነት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኃላፊዎች፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤትና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም