በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ ልማት ስራ እየተከናወነ ነው

135

ነሐሴ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ቢሮ ሃላፊዎች ገለጹ።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ አበራ ወርቁ የእንስሳትን ምርታማነት ለማሳደግ ዝርያ ለማሻሻልና የእንስሳት በቂ መኖ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቦረናን ጨምሮ በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የእንስሳት መኖን በመስኖ ለማልማት የውሃ ግድብ መሰረተ ልማት ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ደረጃቸው ቢለያይም በድርቅ የሚጠቁ ከ10 የማያንሱ አካባቢዎች እንዳሉ ገልፀው፤ በ2015 በጀት ዓመት በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች ከ90 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለመኖ ልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በክረምት ወቅት ቁጥቋጦ አካባቢዎችን በሳር መተካት እንዲሁም በበልግ ዝናብ እና በመስኖ መኖን በማልማት እንደሚከወን ተናግረዋል።

ከመኖ ባሻገርም ለእንስሳት የውሃ አቅርቦት ከወዲሁ ለመስራት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ዓመት በእንስሳት ልማት ከ500 ሺህ በላይ እንስሳትን ለማዳቀል ታቅዶ ከ300 ሺህ በላይ በማዳቀል 68 በመቶውን ማሳካት እንደተቻለም ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር የተቀናጀ ግብርና በምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ገልፀው፤ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብለዋል።

May be an image of 1 person

እንደ አገር 22 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ የወቅቱ ምርት ግን በዓመት ከ7 ቢሊዮን ሊትር እንደማይበልጥ ተናግረዋል።

ክልሉ በእንስሳት ማዳቀል ላይ በስፋት እየሰራ ሲሆን ለዚህም በቤተሰብ ቢያንስ 400 ካሬ ሜትር እንስሳት መኖ አልምቶ ከራሱ አለፎ ለሌሎችም መሸጥ እንዲችል የማድረግ ግብ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በተለይም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የመኖ እጥረት እንዳይከሰት በቂ መኖ የማምረት ስራ በትኩረት ይከናወናል ነው ያሉት።

ለዚህም የተቀናጀ ተፋስስ ልማት የሚሰራባቸው ላይ መልካም ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም