የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም መስክ ዕድገት አሳይተዋል- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

200

ነሃሴ 2/2014/ኢዜአ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም መስክ የተሻለ እድገት ያሳዩበትና በፋይናንስ አፈፃፀማቸውም ጤናማነት የተስተዋለበት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ከባንክ ተወካዮች ጋር በ2014 በጀት ዓመት የዘርፉ አፈፃፀም ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት መልከ ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ቢኖሩም በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት ማስመዝገቧ በመድረኩ ተገልጿል።

መንግስት በፋይናንስ ዘርፍ ባደረገው ሪፎርምና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰዱ በፋይናንስ ሴክተሩ ለውጥ እንደመተዘመገበ ተገልጿል።

ለአብነትም የወለድ አልባ ባንኮች መቋቋም፣ የተንቀሳቃሽ ንብረት የብድር አገልግሎት መፈቀድ፣ የውጭ ዜግነት ያላችው ኢትዮጵያዊያን በባንኩ ዘርፍ እንዲሰማሩ መፈቀዱ፣ የካፒታል ገበያ መፈቀዱና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲያድጉ መደረጉ ተጠቅሷል።

በዚህም የባንኮች ቁጥር በ67 በመቶ፣ የባንኮች ቅርንጫፎች ብዛት በ61 በመቶ፣ ጠቅላላ ሀብታቸው በየዓመቱ በአካማይ 24 በመቶ፣ ተቀማጭ ገንዘብ 93 በመቶ፣ የብድር አቅርቦታቸው 73 በመቶ፣ ጠቅላላ ካፒታላቸው ደግሞ 101 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል።

በመንግስትና በግል ባንኮች የገበያ ድርሻ ረገድም የተቀራረበ እንደሆነ በባንክ እድገት ጤናማነት ሲመዘንም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ በተቀማጭ ገንዘብና በብድር አመላለስ በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ዕድገት በመምጣቱ ባንኮች ውጤታማ አፈፃፀም አሳይተዋልብለዋል።

በተለይም በዲጂታል ባንኪንግ ከፍተኛ ዝውውር መታየቱን በተለይም የቴሌብር ወደ ገበያ መቀላቀል ለዲጅታል ባንኪንግ መነሳሳት ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።

የኤሌክትሮኒክ ግብይት አፈፃፀምም በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች በበርካታ ተገዳሮቶች ውስጥ ሆነው እንኳን ከመደበኛ የባንክ አገልግሎቶቻቸው ባሻገር ማህበራዊ ኅላፊነትቸውን በሚገባ እንደተወጡም ገልጸዋል።

ለአብነትም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከተሰበሰበው ውስጥ ግማሹ ከባንኮች የተሰበሰበ እንደሆነ አንስተዋል።

ምንም እንኳን ባለፉት ዓመታት ባንኮች ያሳዩት ዕድገት በጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም ይበልጥ መሰራት ያላበችውና የወደፊት ስጋቶችን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ከብድር አቅርቦት አንፃር ባንኮች ብድር ከትልልቅ ባለሀብቶችና ከተማ አካባቢ ከመታጠር ተሻግሮ በገጠር ማህበረሰቡንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እና ታችኛውን ማህበረሰብን መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በፋይናንስ ተደራሽነት በተመለከተም ባንኮች ከቅርንጫፍ ከፈታ ባሻገር በሞባይል ባንኪንግና በሌሎች ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች በማስፋት በገጠር ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል በሕገ ወጥነት እና ማጭበርበር ድርጊቶች በመግታት እና ከባንኮች ውጭ በንግዱ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በማሰባበሰብ ባንኮች የአሰራር ስርዓት መዘርጋትና ከህግ አካላት ጋር በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ወደፊት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ቤት ከገቡም አገር በቀል ባንኮች ሰፊ ውድድር ስለሚጠብቃቸው ከወዲሁ ስትራቴጂ ቀይሰው ሊሰሩ አንደሚገባ ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡት የባንክ ስራ አስፈጻሚዎች ባለፉት አራት ዓመታት የመጣው አወንታዊ ውጤት ባንኮች በዲጂታል ባንኪንግ እየዘመኑና አቅማቸውን እያጎለበተቱ ተደራሽነታቸውንም እያሰፉ በመመጣታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በብሔራዊ ባንክ የወጡ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችና ከባንኮች ጋር የተናበበ የቁጥጥር ስራ ለፋይናነስ ዘርፉ ዕድገት አወንታዊ ሚና ነበራቸው ብለዋል።

የውስጥ ደህንነትን ቁጥጥር ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ ማሻሻል፣ በገጠር ተደራሽነትና በብድር አቅርቦት  እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የባንክ ብድርን እስከታችኛው ህብረተሰብ ተደራሽነት ለማስፋትም ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲሁም አስተማማኝ ማንነት ሰነዶች ጉዳይ ሊታሰብብት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በባንኮች የሚስተዋለውን የደንበኞች መታለልና ህገ ወጥ ድርጊት በተመለከተ ባንኮች ሪፖርት በሚያደርጉት መሰረት የፍትህ ተቋማት ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም