አልሸባብ በተደመሰሰባቸው አካባቢዎች ህንጻዎችና ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያወድሙ ፈንጂዎች ተያዙ

150

ነሐሴ 02 ቀን 2014(ኢዜአ) አልሸባብ በተደመሰሰባቸው አካባቢዎች በተደረገ አሰሳ ህንጻዎችና ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያወድሙ ፈንጂዎች መያዛቸውን ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች አልሸባብን በደመሰሱባቸው አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ ቀደም ብሎና በውጊያ ወቅት የቀበራቸው ፈንጂዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ በአሰሳ እየተያዙ መሆኑን ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል፡፡

No photo description available.

የኮማንድ ፖስቱ አባልና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ምክትል ኮሚሽነር ዘከሪያ አብዲ ከሊፍ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሀገር ለመግባት ሞክሮ የነበረውን አሸባሪው አልሸባብን መደምሰሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ወደ መሃል ሀገር ሊገቡ የነበሩ ህንጻዎችና ከባድ ተሽከርካሪዎችን ማውደም የሚችሉ አደገኛ ፈንጂዎችና ተቀጣጣይ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የማፅዳት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ በተደመሰሰባቸው አካባቢዎች በተደረገ አሰሳና በህብረተሰቡ ጥቆማ ከባድ የብረት ፈንጂዎችና ተቀጣጣይ ነገሮች የያዙ ጀሪካኖች መያዛቸውን ጠቅሰዋል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የመሀንዲስ መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ሪያድ ጉሌድ በበኩላቸው የተያዙት ፈንጂዎች ጸረ ሰው፣ ፀረ ተሽከርካሪና ትላልቅ ህንጻዎችን ሊያወድሙ የሚችሉ አደገኛ ተቀጣጣይነት ያላቸው ናቸው ብለዋል።

May be an image of 1 person and outdoors

ፈንጂዎቹ በጋራዥ ውስጥ የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው ጠላት ሳያጠምዳቸው የተያዙና ካጠመዳቸው በኋላም የከሸፉ መኖራቸውን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ጥቅም ላይ ቢያውላቸው ኖሮ ሰፊ ጉዳት ያደርሱ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

አልሸባብ ተሽከርካሪን ለማፈንዳትና መተላለፊያን ለመዝጋት ያዘጋጃቸው ፈንጂዎች እንዲሁም በጀሪካን የፈንጂ መቀመሚያ ባሩድና የውሸት ጥይት የያዘባቸው ቁሳቁሶችም ተይዘዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም