የኢትዮጵያ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለናይጄሪያ ጥሩ ተሞክሮ የሚሆን ነው- የናይጄሪያ ልኡካን

100

ነሃሴ 2/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ክንውን ለናይጄሪያም ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የናይጄሪያ መንግስት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ልኡካን ተናገሩ።

የናይጄሪያ  መንግስት ከፍተኛ  ፖሊሲ አማካሪዎች ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኦሮሚያ ክልል የካቢኔ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

የልኡካን ቡድኑ አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በሼራ ዲባንዲባ ቀበሌ በክላስተር እየለማ የሚገኝ የአቦካዶ ምርትም ጉብኝተዋል።

የልዑክ ቡድኑን የሚመሩት ዶክተር ኢማኑኤል ሳምቦ ማማ፤ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሀመዱ ቡሃሪ የኢትዮጵያን መልካም የልማት ተሞክሮዎች ልምድ እንዲቀስሙ እንደላኳቸው ተናግረዋል።

በጉብኝታቸውም በፍራፍሬ ልማት በተለይም በአቦካዶ ምርት ኢትዮጵያ አስደናቂ እመርታ እያሳየች መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ውዲህ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ከራስ አልፎ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት መመረት መጀመሩ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጥሩ ልምድ የሚገኝበት መሆኑን ጠቅሰው ናይጄሪያም ጥሩ ተሞክሮ ማግኘቷን ተናግረዋል።

ሌላኛው የልዑክ ቡድን አባል ብርጋዴል ጀኔራል ሲለቪስቴር ሊወዴ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አርሶ አደሩ ከራሱ አልፎ  ለገበያ ምርት ማቅረብ እንዲችል የጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የናይጄሪያ መንግስት ከዚህ ጥሩ ተሞክሮ አግኝቷል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና  ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛው የአፍሪካ አገራት  ልምድ ለመቅሰም ወደ ምዕራባዊያንና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት እንደሚያማትሩ አስታውሰው ለአህጉሪቷ ልማት በውስጥ በርካታ ልምዶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ በህዝብ ብዛትና በምጣኔ ሀብቷ አንደኛ የሆነችው ናይጄሪያ በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወነ ስላለው ልምድ ለመጋራት መፈለጓ ቀጣይ በትብብር ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የናይጄሪያ  መንግስት ከፍተኛ  የፖሊሲ አማካሪዎች ልዑካን ቡድን አባላት ከጉብኝታቸው ባሻገር የአረንጓዴ አሻራቸውን በሼራ ዲባንዲባ ቀበሌ አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም