የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ለማስተዋወቅ ሀላል የምግብና ቱሪዝም አውደ ርእይ የላቀ ሚና ይኖረዋል- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

223

ነሐሴ 02 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ለማስተዋወቅ ሀላል የምግብና ቱሪዝም አውደ ርእይ የላቀ ሚና የሚኖረው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ ፡፡

ከኢድ እስከ ኢድ መርሃ ግብርአካል የሆነው የሀላል ምግብና የቱሪዝም አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር  ብርቱካን አያኖ፤ የዓውደ ርዕዩ ዋነኛ አላማ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በቱሪዝም እና በወጭ ንግድ ዘርፍ ያላትን አማራጭ ለማስፋትና ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ የውጪ ሀገራት ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ሌሎችም የሚገኙበት በመሆኑ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ለማስተዋወቅ ሀላል የምግብና ቱሪዝም አውደ ርእይ የላቀ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ፤ የኢትዮጵያን የባህል እሴቶች፣  ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብቶችን ለቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ አውደ ርእዩ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

May be an image of 6 people, people sitting, people standing and indoor

በመሆኑም በቀጣይ እንደ ሃላል አይነት መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለአገር አድገት የማይተካ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ለዚህም እንደ ሀላል አይነት ምግብና የቱሪዝም አውደ ርዕይ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአውደ ርእዩ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ሌሎችም የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ ባለደርሻ አካላት ታድመዋል።

የተለያዩ ሆቴሎች፣ ስጋ አምራቾች፣ አስመጪና ላኪዎች እንዲሁም የገበያ ማዕከላት በአውደ ርእዩ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም