የግብርና ምርታማነታቸው ከፍ ያሉና በሽታን መከላከል የሚችሉ ምርጥ የሰብል ዝርያዎች በ16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተባዙ ነው

88

ነሐሴ 02 ቀን 2014(ኢዜአ) ምርታማነታቸው ከፍ ያሉና በሽታን መከላከል የሚችሉ የተለያዩ ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በ16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማባዛት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሸን ገለጸ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ክፍሌ ወልደ ማርያም፤ አርሶ አደሩ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ በሚያደርገው የእርሻ እንቅስቃሴ ውስጥ ኮርፖሬሽኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እርሻን መካናይዝ የሚያደርጉ እንደ ትራክተር፣ ኮምባይነርና ፓምፕ የመሳሰሉ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በሄክታር ምርታማነታቸው ከፍ ያሉና በሽታን መከላከል የሚችሉ ምርጥ የሰብል ዘሮችን፣ የአረም መከላከያ መድሃኒቶችን፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሩ በማድረስ ለግብርናው የራሱን አስተዋጽኦ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም መንግስት ያቀደውን በምግብ ፍጆታ ራስን ከመቻል ባሻገር ወደ ሌሎች አገራት የመላክ ዕቅድ እንዲሳካ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በአነስተኛ መሬት ላይ ከፍ ያለ ምርት የሚሰጡ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመኸሩ ምርታማነታቸው ከፍ ያሉና በሽታን መከላከል የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን በ16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማባዛት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

ከዚህም 300 ሺህ ኩንታል ዘር በማግኘት ለበጋ መስኖና ለመደበኛ መስኖ የዘር ፍጆታ ለማዳረስ ታስቧል ብለዋል።

በኮርፖሬሽኑ አሰላና የአርዳይታ ምርጥ ዘር እርሻ ልማት ስራ አስፈጻሚዎች በሰጡት አስተያየት ያላቸውን የእርሻ መሬቶች በዘር በመሸፈን የሰብል እንክብካቤ ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ የክረምት ወቅት ያለው የአየር ጠባይም ጥሩ የሚባል በመሆኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሸን 25 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትና ጣቢያዎች ያሉት የመንግስት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም