አደንዛዥ እጽ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል-ፖሊስ

153

ጎንደር፣ ነሃሴ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ 52 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙኒክሽን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት አደንዛዥ እጹ በከተማው ቀበሌ 01 ልዩ ቦታው ብልኮ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ዛሬ ተይዟል ።

አደንዛዥ እጹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ1- 20870 አ.ማ በሆነ ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ በድብቅ ተጭኖ ሲጓጓዝ መያዙን ተናግረዋል ።

የባጃጅ አሽከርካሪውን ጨምሮ አደንዛዥ እጹን ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ክትትል አደንዛዥ እጹ መያዙን ገልጸዋል ።

ህብረተሰቡ ለፖሊስ ስለሰጠው ጥቆማ አመስግነው በቀጣይም የተለየ ነገር ሲያጋጥም የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል ።

በከተማው በሚስተዋለው የእፅ ዝውውር ትውልዱን ከሱስ ተጋላጭነት ለመታደግ ወንጀሉን ከመከላከል ጎን ለጎን ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢውን ክትትል በማድረግ ደህንነታቸውን የመጠበቅ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም