ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ዘርፉን በእውቀትና በቁርጠኝነት መምራት ይገባል

64

ሰመራ ነሀሴ 2/2014 (ኢዜአ) ኢኮኖሚዉ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዘርፉን በእውቀትና በቁርጠኝነት መምራት እንደሚገባቸው የአፋር ክልል ርእሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስገነዘቡ።

በክልሉ በ2014  የገቢ አሰባሰብ እቅድ አፈጻጸምና በ2015 በጀት አመት እቅድን በተመለከተ ከወረዳ አመራሮች ጋር በሰመራ ከተማ ምክክር ተካሂዷል።

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጫቸው የተለያዩ የገቢ አማራጮች አሉ።

ይሁንና እስካሁን በክልሉ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በዋናነት ከስራ ግብር፣ከጨው ምርትና ከሚታወቁ የገቢ አርእስቶች እንደሆነ ተናግረዋል ።

በተለይም የህብረተሰቡ የኢኮኖሚ መሠረት ከሆነው የቁም እንስሳትና የመሬት መጠቀሚያ ግብርን ጨምሮ የመዘጋጃ ቤትና ተያያዥ  የገቢ አሜራጮች ላይ ትኩረት በመስጠት መሰብሰብ አንደሚገባ አመልክተዋል።


ለተግባራዊነቱም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዘርፉን በእውቀትና በቁርጠኝነት ከፊት ሆኖ መምራት ተቀዳሚ ተልእኳቸው አድርገው መውሰድ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ሀሰን በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ለውጡን ተከትሎ  የገቢ ሴክተሩ ላይ ባከናወነው ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ከ800 ሚሊዮን ብር አልፎ የማያውቀው ክልላዊ ገቢ ባለፉት አራት አመታት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አመልክተዋል።

በአመታቱ የገቢ አሰባሰቡ ከ270 በመቶ  በላይ እድገት ማሳየቱን ጠቁመው  ይሁንና በክልሉ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ የመሰብሰብ አቅም አኳያ ብዙ የሚቀረው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ በክልሉ በ2015 በጀት አመት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን አመላክተዋል።

ለመሰብሰብ የታቀደው ገቢ በ2014 በጀት አመት ከተሰበሰበው ከ41 በመቶ በላይ ጭማሪ አንዳለው ጠቅሰዋል።

"እቅዱን ለማሳካት በዋናነት ታችኛው መዋቅር ላይ የሚገኙ የገቢ አቅሞችን በአግባቡ ለመሰብሰብ አመራሩ ዘርፉን የህልውና ጉዳይ አድርጎ በሃላፊነት መምራት ይጠበቅበታል" ብለዋል

የያሎ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እስማኢል ከድር በወረዳው በአብዛኛው ከሰራተኛ ግብር ውጭ ያሉ የተየያዩ ገቢ አርእስቶችን በአግባቡ የመሰብሰብ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ክፍተቱን በማረም የተለያዩ የገቢ አማራጮችን በመለየት የሚጠበቀውን ገቢ ለመሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

"የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የሚቻለው ገቢን ማሳደግ ሲቻል ነው " ያሉት ደግሞ  የተላላክ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ነኢማ አሊ ናቸው።

በወረዳው ከመሬት መጠቀሚያና የቁም እንስሳት ግብር ጨምሮ የተለያዩ የገቢ አማራጮችን እስከታች ወርዶ የመሰብሰብ ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም