የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

105
ዲላ መስከረም6/2011 በዲላ ከተማ የመሠረት ልማት ችግሮች እንዲፈቱ ቁጥጥርና ክትትላቸውን በማጠናከር ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ችግሮችን አመልክቶ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት እንዳሉት ዓመታትን የዘለቁ  የመሰረተ ልማት ችግሮች  ለመፍተት ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ችግሮቹን በተያዘው የበጀት ዓመት እንዲፈቱም የተሰጣቸውን የህዝብ ውክልና በመጠቀም አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጠርና በመከታተል ድጋፋቸውን እንደሚጠናክሩ ተናግረዋል ፡፡ ከአባላቱ መካከል ወይዘሮ ኡፋይሴ መልካሙ በከተማዋ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች በአስተዳደሩ ትኩረት አግኝተው እንዲፈቱ በምክር ቤቱ አማካይነት ሲታገሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል ፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ የመሰረተ ልማት ችግሮች መካከል የመንገድ ዳር መብራትና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ ከተማዋ ዋናውን መንገድ ጨምሮ አብዛኛው ጎዳናዎቿ ማታ ማታ ብርሀን አልባዎች በመሆናቸው ምሽት የሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎች ለዝርፊያና ሌላም ጥቃቶች መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡ የከተማዋ መንገዶች ማታ ማታ ስለሚጨልሙ በሞተር ተንቀሳቅሰው ለሚቀሙና ጨለማን ተገን በማድረግ ዝርፊያ ለሚፈፅሙ ወንጀለኞች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለመገንባታቸውም ህብረተሰቡን ለእንግልት ከመዳረጋቸው ባለፈ ወደጤና ተቋማት እንደልባቸው ለመንቀሳቀስ አዳጋች እንደሆናባቸው ነው ወይዘሮ ኡፋይሴ ያስረዱት፡፡ እነዚህ ለረጅም ጊዜ የህብረተሰቡ ጥያቄ ሆነው የቆዩ የመሰረተ ልማት ችግሮች በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንዲያገኙ እንደ ነዋሪው ተወካይነታቸው በምክርቤቱ አማካይነት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ግፋወሰን ገብሬ በበኩላቸው በተለይ ያልተከፈቱ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች ነዋሪዎችን ሲያስመርሩ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ " የምክር ቤት አባላት እንደ ከተማው ነዋሪዎች ተወካይነታችን የህብተሰቡን ችግር የመለየትና አመራሩ ትኩረት እንዲሰጠው የማድረግ ኃላፊነት አለብን " ብለዋል፡፡ በከተማዋ በስፋት የሚታዩ የውስጥ ለውስጥ መንገድና የመንገድ ዳር መብራት ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው በተያዘው ባጀት ዓመት እልባት እንደሚያገኝ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ በከተማዋ የመሠረተ ልማት ችግር መኖሩን መገምገማቸውን የተናገሩት ደግሞ የምክር ቤቱ የመሠረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ   አቶ ወርቃገኘው በየነ ናቸው፡፡ አቶ ወርቃገኘው እንዳመለከቱት ከመሰረተ ልማት እጥረት ባሻገር የተገነቡ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶችም ተገቢውን ቁጥጥርና  የማስተዳደር ሥራ የላቸውም፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ችግሮቹን ለመፍታት የወሰዳቸው እርምጃዎች ቢኖሩም ህብረተሰቡን ለማርካት በሚያስችል መልኩ አይደለም ፡፡ " የነዋሪዎችን ቅሬታዎች በየሩብ ዓመቱ ወደ አስተዳደር አካላት ይዘን በመሄድ እንዲፈቱ ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል፡፡ የከተማዋ  አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አልማሰን የከተማዋ ህዝብ የሚያነሳቸው  የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንዳሉ አምነዋል፡፡ የመንገድ መክፈት ስራው አስቸጋሪ ከሚያደርጉ  መካከል አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ጥቅጥቅ ባለ ቋሚ ሰብል መሸፈኑ ይህም ለመንገድ ግንባታ ለሚነሱ ሰብሎች የሚከፈል ከፍተኛ የካሳ መጠን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት በተመደበው   አነስተኛ በጀት ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መከፈቱን ጠቅሰው  በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 30 ኪሎ ሜትር በላይ በተመሳሳይ ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል፡፡ 20 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ ደረጃቸውን ለማሻሻል እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ በተያዘው የበጀት ዓመት ሌሎችንም የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት በትኩረት  እንደሚሰራ ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም