በሰለጠኑበት መስክ ህዝባቸውን በቅንነት እንደሚያገለግሉ ተራቂዎች ገለጹ

47
ሆስዕና መስከረም 6/2011 በሰለጠኑበት የጤናው መስክ ህዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት እንደሚያገለግሉ የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ትምህርት ኮሌጅ  ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ኮሌጁ ያሰለጠናቸውን 342 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡ ተመራቂ ተዘራ አብርሃም በኮሌጁ በጤናና መረጃ ትምህርት ክፍል የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆነ " ቃል በገባሁት መሰረት ለሃገሬ በጤናው ዘርፍ የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ " ሲል ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡ በሰለጠነበት መስክ  ህዝቡን በታማኝነትና በቅንነት እንደሚያገለግልም ተናግሯል፡፡ "በአንድነት ለሃገር እድገት ሁሉም በሚረባረብበት ወቅት በመመረቄ እድለኛ ነኝ " ያለችው ደግሞ በአዋላጅ ጤና መኮንንት የተመረቀችው  አስቴር ሃብቴ ናት፡፡ ከእሷ የሚጠበቀውን ለህዝቧ በማድረግ የሀገሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ተናግራለች፡፡ ለወላድ እናቶች ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ በመከታተልና በመርዳት እናቶችንና ህፃናትን ከሞት ለመታደግ  እንደምትሰራም ገልጻለች፡፡ በአዋላጅ ጤና መኮንን የማዕረግ ተመራቂዋ ወርቅነሽ መንግሰቱ በበኩሏ ብዙ እናቶች በህክምና እጦትና ደም በመፍሰስ  ምክንያት ህይወታቸው እንዳያልፍ እሰራለሁ ብላለች፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ መለሰ ዘውገ ተመራቂዎቹ ከደረጃ ሶስት እስከ ደረጃ አራት ትምህርታቸውን የተከታተሉ 342 ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጤና ባለሙያ መሆን የመንግስት ሰራተኝነት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መኖር እንደሆነ የገለጹት ደግሞ  የደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር አብርሃም አላኖ ናቸው፡፡ ተመራቂዎች  የቀሰሙትን ትምህርት በተግባር ላይ በማዋል ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት መገልገል እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም