የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት የሚያላቅቁ 81 የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

75

አዳማ ነሀሴ 02/2014 /ኢዜአ/ የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት የሚያላቅቁ 81 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በ13 ቢሊዮን ብር እየተገነቡ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ ።

የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ድርቅ በክልሉ በእንስሳት ሀብትና በሰብል ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል ።

በተለይ በቦረና;ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ;ምስራቅ ባሌና ባሌ ዞን;ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ የተከሰተው ድርቅ አሁንም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል ።

ይሄንን ችግሮች መቋቋም የምንችለው የተፈጥሮ ዝናብ በመጠበቅ ሳይሆን አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት ግድቦችን በስፋት በመገንባት በበጋው ጭምር ሰብልና የእንስሳት መኖን በብዛት ማምረት ስንችል ነው ብለዋል ።

ለዚህም የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት በ13 ቢሊዮን ብር ወጪ 81 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጄክቶች እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል ።

የፕሮጄክቶቹ ግንባታቸው በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቆ ለተፈለገው አገልግሎት እንዲውሉ ለማስቻል ጠንካራ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል ።

ይህም ድርቁ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ ከመቋቋም ባለፈ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በዘላቂነት ከተረጂነት ለማላቀቅ ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ያሉ ለም መሬቶችን ወደ ልማት ለማስገባት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ አርብቶ አደሩ በብቸኝነት ከያዘው የእንስሳት ሀብት ልማት በተጨማሪ ወደ ከፊል አርሶ አደር ለማሻገር ግብ አስቀምው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል ።

የክልሉ መንግስት በቀጣይ አራት ዓመታት ከ250 በላይ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለመገንባት አቅዶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።

በዚህም የክልሉን ግብርና ከተፈጥሮ የዝናብ ጥገኝነት ከማላቀቅ ባለፈ በሁሉም ዞኖች በበጋ ወቅት ከስንዴ በተጨማሪ ሌሎች ዋና ዋና ሰብሎችና የእንስሳት መኖን ለማልማት ጭምር ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም